በኢትዮጵያ በወጭ ንግድ ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የታቀደው የውጭ ምንዛሪ በየአመቱ እየቀነሰ ነው

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 23/2009) በኢትዮጵያ በወጭ ንግድ ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የታቀደው የውጭ ምንዛሪ በየአመቱ እየቀነሰ መቀጠሉ ታወቀ።

ለዚህ አመት ይገኛል ተብሎ በእቅድ ከተቀመጠውም የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ቅናሽ መታየቱንም የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ሳይቋረጥ 11 በመቶ እያደገ መሆኑ ለ10 አመት ያህል እየተነገረ ነገር ግን የወጭ ንግድ እያሽቆለቆለ መቀጠሉ ብርቱ ጥያቄን እያስነሳ ይገኛል።

በዚህ አመት ማለትም በ2009 በጀት አመት በወጭ ንግድ የገኛል ተብሎ የተጠበቀው 4 ነጥብ 75 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መሆኑን የገለጸው የንግድ ሚኒስቴር የተገኘው ግን 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መሆኑን አስታውቋል።

ይህም ይገኛል ተብሎ ከታቀደው የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ልዩነት እንዳለውም አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በወጭ ንግድ ካገኘቸው 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ከፍተኛው ገቢ የተገኘው እንደተለመደው በቡና ንግድ እንደሆነም ተመልክቷል።

ሆኖም በቡና ይገኛል ተብሎ የተጠበቀው ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም የተገኘው 882 ነጥብ 47 ሚሊየን ዶላር ሲሆን ይህም ከእቅዱ የ58 ሚሊየን ዶላር ልዩነት ተመዝግቦበታል።

በጫት ንግድ ከ48 ሺ ቶን በላይ ወደ ውጭ በመላክ ከእቅዱ በላይ 272 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ያብራራው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ በሰሊጥ ምርትም የተገኘው ገቢ ከተጠበቀው በታች እንደሆነ አመልክቷል።

ባለፈው በ2008 የኢትዮጵያ በጀት አመት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ብቻ እንደነበርም ማስታወስ ተችሏል።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በወጭ ንግድ ውስጥ ያላት ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ የተመዘገባ ሲሆን ይህም ይበልጥ እየተንሸራተተ መቀጠሉ አነጋጋሪ ሆኗል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የወጭ ንግድ እንቅስቃሴዎችን በመዳሰስ የወጡ ሪፖርቶች እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ በወጭ ንግድ በምታገኘው ገቢ ከአለም 123ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዝቅተኛ የወጭ ንግድ ካላቸው ሀገራት በአለም ላይ ዝቅተኛ ሆነው ከኢትዮጵያ በታች የተመዘገቡት ሀገራት አፍጋኒስታንና ጋምቢያ ብቻ ናቸው።–ኢትዮጵያ ከስር በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ የወጭ ንግድ ደረጃ 9 ነጥብ 8 በመቶ ሲሆን መንግስት አልባዋ ሶማሊያ እንኳን የወጭ ንግድ ድርሻዋ 14 ነጥብ 5 በመቶ ነው።

በአለም ላይ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የወጭ ንግድ ድርሻ ከ10 በመቶ በታች የሆነባቸው ሀገራት አፍጋኒስታን፣ጋምቢያና ኢትዮጵያ ናቸው።

የኢትዮጵያ የወጭ ንግድን ሶስት ቢሊየን ዶላር ማድረስ ባልተቻለበት በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በግማሽ የምታንሰው ኬንያ በወጭ ንግድ ወደ 6 ቢሊየን ዶላር እያገኘች ሲሆን ደቡብ አፍሪካ 81,ናይጄሪያ 45 እንዲሁም ግብጽ 20 ቢሊየን ዶላር በወጭ ንግድ ያገኛሉ።