በአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ታሪፍ ላይ ጭማሪ ሊደረግ ነው

(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 23/2009) በአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ታሪፍ እንዲጨምር የአዲስ አበባ ምክር ቤት ወሰነ።

በምግብ እህሎችና በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተመዘገበ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በውሃ ላይ የታሪፍ ጭማሪ መደረጉ በከተማዋ ነዋሪ ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረውም እየተገለጸ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ውሃውን ከማመርትበት የምሸጥበት ዋጋ ያነሰ በመሆኑ ለመጨመር ተገድጃለሁ ማለቱም ተመልክቷል።

አንድ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወይንም አንድ ሺ ሊትር ውሃን አጣርቶ ለተጠቃሚ ለማቅረብ 6 ብር እንደሚጠይቅ የገለጸው የከተማዋ የውሃ አቅራቢ ተቋም አንድ ሺህ ሊትሩን ከማምረቻ ዋጋው በግማሽ በሶስት ብር ሲሸጥ መቆየቱንም ዘርዝሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተወሰነው የታሪፍ ጭማሪ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ያልተገለጸ ሲሆን የጭማሪውም መጠን አልታወቀም።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በየቀኑ 600 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ለነዋሪው እንደሚያቀርብ ቢናገርም ከዚህ ውስጥ 30 በመቶው እንደሚባክንም ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማን ህዝብ የውሃ ፍላጎት ለማሟላት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያስፈልግ በጥናቶች ተረጋግጧል።

በኢትዮጵያ የሸቀጦች እንዲሁም የምግብ ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የውሃ ታሪፍ ጭማሪው በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ ተጨማሪ ጫና እንደሚፈጥርም ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

የጤፍ ዋጋ 3 ሺህ ብር የገባ ሲሆን የሌሎች ምርቶች ዋጋ ጨምሯል።የብሩም የመግዛት አቅም እየወረደ መምጣቱንም መረዳት ተችሏል።