በጣሊያን መዲና በኢትዮጵያውያንና በጣሊያን ፖሊስ መካከል በተፈጠረው ግጭት የተጎዳ ኢትዮጵያዊ የለም መባሉ በርካቶችን ማስቆጣቱ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 23/2009) በጣሊያን መዲና በኢትዮጵያውያንና በጣሊያን ፖሊስ መካከል በተፈጠረው ግጭት የተጎዳ ኢትዮጵያዊ የለም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ በርካቶችን ማስቆጣቱ ታወቀ።

በሮም የሚገኘው ኤምባሲው በቦታው ተገኝቼ ባደረኩት ማጣራት አራት ኢትዮጵያውያን ከህንፃው በሰላማዊ መንገድ ሲወጡ አይቻለሁ በማለት የሰጠው ምስክርነትም በርካቶችን አስገርሟል።

ከዚህ ውጭ የሌሎች አፍሪካውያን አገራት እንጂ የጉዞ ሰነድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በቦታው አልነበሩም ሲል የሰጠውን ምስክርነትም ከእውነት የራቀ ሲሉ በጣሊያን ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን አጣጥለውታል።

በህወሃት መንግስት በኩል የተሰጠው መግለጫ፡ ከተጎዱት ዜጎች ይልቅ ለጣሊያን መንግስት መቆርቆርን ያሳየ ነው የሚልም ተቃውሞ ቀርቦበታል።

ባለፈው ሳምንት የበርካታ የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የወሰደ ክስተት ነበር።

ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከሚኖሩበት ህንጻ በድንገት እንዲለቁ በፖሊስ የተወሰደው የሃይል እርምጃን ተከትሎ የጣሊያን ፖሊስ ላይ ከውስጥም ከውጭም ተቃውሞ መቅረቡ ይታወሳል።

በህገወጥ መንገድ የተያዘውን ህንጻ ለባለቤቱ እንዲመለስ መደረጉና ለአራት ዓመት ህንጻውን በመኖሪያነት የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በአስገዳጅ ሁኔታ በሌሊት እንዲወጡ መደረጉ በጣሊያን የሞቀ ክርክር እንዲፈጠር አድርጓል።

በስልጣን ላይ ባለው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መሃል በፓርላማ ሳይቀር ከፍተኛ ሙግት መካሄዱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለይም ኢትዮጵያውያኑና ኤርትራውያኑ ከህንጻው በሃይል እንዲለቁ ከተደረጉ በኋላ በጊዜያዊነት ካረፉበት ጎዳና ላይ እንዲነሱ በፖሊስ በኩል የተወሰደ እርምጃ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር በመገናኛ ብዙሃን የተመለከቱትን ሁሉ ያስቆጣ እንደነበረ ተገልጿል።

ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች ጉዳዩ የሰብዓዊ መብት የሚጨፈልቅ በመሆኑ የጣሊያን መንግስት በአስቸኳይ እንዲመረምረው መጠየቁ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያውያኑ በሃይል ከህንጻው እንዲለቁ ከተደረጉበት ዕለት አንስቶ በአደባባይ ኢሰብዓዊ እርምጃ ሲወሰድባቸው ድምጹን አጥፍቶ የሰነበተው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያወጣው መግለጫ በእርግጥ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኗል። በጣሊያን በጉዳት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የበለጠ ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ለኢሳት የደርሱ መረጃዎች አመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው እንዳለው በጣሊያን መዲና በኢትዮጵያውያንና በጣሊያን ፖሊስ መካከል በተፈጠረው ግጭት የተጎዳ ኢትዮጵያዊ የለም።

መግለጫው በመቀጠል በጣልያን ርዕሰ መዲና ሮም ልዩ ስሙ ተርሚኒ በተባለ የከተማው ስፍራ የአንድ የግለሰብ ህንፃ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ለአራት ዓመት ያህል ሲኖሩ የነበሩ ስደተኞች ቤቱን ለባለቤቱ እንዲመለስ ፍርድ ቤት በመወሰኑ፣ ፖሊስ ለማስወጣት ባደረገው ጥረት ወደ ግጭት አምርቷል ሲል በጣሊያን መንግስት ፖሊስ የተሰጠውን መከላከያ ተቀብሎ አስተጋብቷል።

በጣሊያን የሚገኘው ኤምባሲ ወዲያው በቦታው ተገኝቶ ባደረገው ማጣራት አራት ኢትዮጵያውያን ከህንፃ በመውጣት ያለምንም ጉዳት ወደ ሌላ ስፍራ የሄዱ መሆኑን ለማረጋገጥ ችያለሁ ሲል በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ከዚህ ውጭ የሌሎች አፍሪካውያን ሀገራት እንጂ የጉዞ ሰነድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በቦታው አልነበሩም በማለት ከ500በላይ ኢትዮጵያውያንን እንደማያውቃቸው ገልጿል።

ኢሳት ያነጋገራቸውና በሮም ጎዳና ላይ ወድቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በህወሀት መንግስ መግለጫ ተቆጥተዋል።

የተጎዳነው በአደባባይ እየታየ የተጎዱ የሉም ማለት ምን ማለት ነው ሲሉም ይጠይቃሉ። በቪዲዮ ምስል በዓለም ዙሪያ የተበተነውን ክስተት የተመለከቱ በእርግጥ በህወሀት መንግስት መግለጫ ግራ መጋባቱ አይቀርም። ኢትዮጵያውያኑ ይናገራሉ።

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ በህንጻው ላይ የሚኖሩ የማያውቃቸው አራት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነው።
ሌሎቹ የጉዞ ሰነድ የሌላቸው በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ማረጋገጫ እንደሌለው የሚመስል ምላሽ ነው የሰጠው።

እነዚህ አራት የተባሉት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በህንጻው ላይ በህገወጥ መንገድ ይኖራሉ ከተባሉትና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚሰሩ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች እንደሆኑ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

ይህም የህወሃት መንግስት በኢትዮጵያዊነት የሚቀበላቸው የስርዓቱን ደጋፊዎች ብቻ መሆኑን ያመላከተበት ነው ብለዋል ታዛቢዎች።

በሮም ጎዳና ላይ ወድቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቀድሞውኑ ከኤምባሲው የሚጠብቁት ነገር እንደሌለ፡ ኤምባሲ አለም ብለው አስበው እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት።

በሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ ስቃይና መከራ ሲደርስባቸው፡ ‘’ግብግብ ለመፍጠር የሞከሩት ላይ የሳውዲ አረቢያ ፖሊስ እርምጃ ወስዷል’’ በማለት አስገራሚ ምልሽ የሰጡት በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን አስታውሰዋል።

በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለኢትዮጵያውያን ምንም አይነት ርህራሄ የሌለው በየሀገራቱ የሚገኙት የኢትዮጵያ ተብለው የሚጠሩት ኤምባሲዎችም በዘር መስመር ላይ በመቆም ለአንድ አካባቢ ተወላጆች አገልግሎት በመስጠት ሌላውን ኢትዮጵያዊ ያገለሉ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ኤምባሲ የለንም የሚሉ ድምጾች ከተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ የሚሰማ ድምጽ ሆኗል።