በግብጽ የፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በየፊናቸው ወደ ካይሮ ጎዳናዎች መውጣታቸውን ቢቢሲ ዘገበ

ሰኔ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ቢቢሲ  እንዳለው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ  የፕሬዚዳንት ሙርሲ ደጋፊዎች ፤ የፕሬዚዳንቱ ሹመት 1ኛ  ዓመት ከሚከበርበት ከሁለት ቀናት በፊት   በናስር ቀጠና በሚገኘው በዋናው መስጊድ መሰባሰብ ጀምረዋል።

በ አንፃሩ የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች  በመጪው እሁድ ከፍ ያለ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ በተለያዩ የካይሮ ጎዳናዎች መሰባሰብ መጀመራቸውን  የዜና አውታሩ አመልክቷል።

በግብጽ ሁለተኛ ከተማ በአሌክሳንደሪያ. በተቃውሞ ሰልፈኞቹና በሙስሊሞች መካከል ግጭት መፈጠሩም ተገልጿል።

በግጭቱ ጥቂት ሰዎች የተጎዱ ሲሆን፤ በሙስሊም ብራዘር ሁድ የሚደገፈው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሻርኪያ ወደተባለ ሰሜናዊ ቦታ  ፔትሮል ቦምብ ተወርውሯል ብሏል።

ትናንት  ሐሙስ ማምሻውን በሰሜናዊ የግብጽ ግዛት በተፈጠረ ግጭትም  አንድ ሰው መሞቱና እና በርካታዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።.

በመዲናዋ በካይሮና በሌሎች በርካታ አካባቢዎች  የደህንነት ሠራተኞች ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ከመሆናቸውም ባሻገር የመከላከያ ሠራዊት አባላትም  በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ተደርገዋል።

ተቃዋሚዎቹ፤ ወደ ስልጣን ከወጡ በመጪው እሁድ  አንድ ዓመት የሚሆናቸውን ፕሬዚዳንት ሙርሲን ከስልጣናቸው እንዲለቁ  በከፍተኛ ሰልፍ ለመጠየቅ እየተዘጋጁ ባሉበት ጊዜ ነው የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ቀድመው የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ወደ አደባባይ የወጡት።

ሙስሊም ብራዘር ሁድ እና አጋሮቹ  ዛሬ አርብ በናስር ከተማ በሚገኘው በራባ አል-አዳዊያ መስጊድ መግቢያ ላይ በከፍተኛ ደረጃ መሰባሰብ መጀመራቸው ተመልክቷል።

ፕሬዚዳንት ሙርሲ ረቡዕ በባደረጉት ንግግር  የኛ መከፋፈል ግብጽን ሽባ ያደርጋታል ማለታቸውን ቢቢሲ አስታውሷል።