ሼህ ዳሂር አዌይስ እጃቸውን እንዲሰጡ ለማግባባት እየተሞከረ ነው

ሰኔ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ከአልሸባብ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሼህ ዳሂር አዌይስ ከሌሎች መሪዎች ጋር ልዩነት መፍጠራቸውን ተከትሎ ጋልምዱግ እየተባለ ወደ ሚጠራው አካባቢ ማቅናታቸው ታውቋል።

የአካባቢው የጎሳ መሪዎችም ሼህ ዳሂርን በስልጣን ላይ ላለው የሶማሊያ መንግስት እጃቸውን እንዲሰጡ ለማግባባት እየሞከሩ ሲሆን፣ ሼሁ ግን እጃቸውን ለመስጠት እስካሁን ፈቃደኛ አልሆኑም። በስልጣን ላይ ላለው መንግስት እውቅና እንደማይሰጡም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሼህ ዳሂር መያዛቸውን ቢገልጽም፣ ቢቢሲ ዛሬ ባቀረበው ዘገባ ግን ግለሰቡ እጃቸውን እንዲሰጡ ለማግባባት እየተሞከረ መሆኑን ገልጿል።

ሼክ ዳሂር እጃቸውን የማይሰጡ ከሆነ ምናልባትም በኢትዮጵያ ወታደሮች ሊያዙ ይችላሉ ወይም ከአካባቢው አምልጠው ወደ ጎረቤት አገር ሊሰደዱ ይችላሉ።

የአሜሪካ መንግስት ሼክ ዳሂርን በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወቃል።