በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አዘጋጅነት ትናንት ቼክ ሪፐብሊክ ኦስትራቫ ውስጥ በተካሄደ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አኩሪ ድል ተቀዳጁ

ሰኔ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በሴቶች የ10 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 30 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ከ 67 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት ቀድማ በመግባት ስታሸንፍ፤ ኬኒያዊቷ ግላዴስ ቼሬኖን 30 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ ከ23 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመጨረስ 2ኛ፣ ሌላዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይነሽ ኦልጂራ ሶስተኛ፣ በመሆን ማጠናቀቃቸው ታውቋል።

በዚሁ ውድድር ላይ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ  ከአምስት ዓመታት በፊት በራሷ ተይዞ የነበረውን የስፍራውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸንፋለች፡፡  ጥሩነሽ በ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት መሆኗ ይታወቃል።
በ800 ሜትር የወንዶች ውድድርም እውቁ ኢትዮጵያዊ የአጭር ርቀት ኮኮብ አትሌት መሀመድ አማን 1 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ78 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ሲያሸንፍ፣ ሩሲያዊው አንድሬ ኦሊቨር 2ኛ፣ ኬንያዊው አንቶኒ ቸሙት ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

መሃመድ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርቀቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነትን ያገኘ ጠንካራ አትሌት ሲሆን የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ጨምሮ በዚህ ዓመት የተካፈለባቸውን ውድድሮች አብዛኞቹን በአሸናፊነት ማጠናቀቁ ይታወሳል።

በ800 ሜትር የወንዶች ውድድርም እውቁ ኢትዮጵያዊ የአጭር ርቀት ኮኮብ አትሌት መሀመድ አማን 1ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ከ78 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ሲያሸንፍ፣ ሩሲያዊው አንድሬ ኦሊቨር 2ኛ፣ ኬንያዊው አንቶኒ ቸሙት ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

መሃመድ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርቀቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነትን ያገኘ ጠንካራ አትሌት ሲሆን የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ጨምሮ በዚህ ዓመት የተካፈለባቸውን ውድድሮች አብዛኞቹን በአሸናፊነት ማጠናቀቁ ይታወሳል።
በ5000 ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊው ሙክታር ኢድሪስ በ13 ደቂቃ 03 ሰከንድ 69 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት አንደኛ ሆኖ ሲያሸንፍ፣ ኬንያውያኑ አውስቲን ቾጌ እና ላዊ ላላንግ እንደቅደም ተከተላቸው 2ኛና ሶስተኛ በመሆን ጨርሰዋል። በዚህ ውድድር እንደሚያሸንፍ አስቀድሞ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሳይሳካለት በ4ኛነት ማጠናቀቁ ታውቋል።
በሴቶች የ3ሺህ ሜትር መሰናክል ኬንያዊቷ ሚልካ ቼሞስ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያዊቷ ህይወት አያሌው 2ኛ፣ ኬንያዊቷ ኩሪቲ ኩዊይ ሶስተኛ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት እቴነሽ ዲሮ ደግሞ አራተኛ ሆና ጨርሳለች።
በሌሎች ርቀቶች ከተካፈሉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል በሴቶች የ1ሺህ ሜትር ውድድር ቃልኪዳን ገዛኸኝ 4ኛ ሆና መጨረሷ ታውቋል