በግብር እዳ የሚማረሩ ነጋዴዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

ጥቅምት (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-‹በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ከገቢያቸው ጋር በማይመጣጠን የግብር  እዳ እየተሰቃዩ  ነው።

የገዢው ፓርቲ ባለስልጣኖች አድሎአዊ በሆነ መልኩ በሚጥሉት ግብር ነጋዴዎች ድርጅታቸውን እየዘጉ ነው። በእነብሴ ሳር ምድር   ወረዳ አሰፋ ሁነኛው፣ ኢሳየ ቸኮል፣ የንጉስ ዋለና  መሰሉ የሚባሉት ነጋዲዎች በጋራ ለቤት መስሪያ በባንክ ከስያዙት  ገንዘብ ላይ ያለፍላጎተቻው በቀላጤ ብቻ ለግብር በሚል

ገንዘባቸው ተወስዷል።

በባህርዳር ከተማ ቀበሌ አስራ ሶስት የሚገኙ ነዋሪዎች በአከራይ ተከራይ የግብር ጥያቄ ቤት ባልሰሩበት አመታት ሁሉ ግብር እንዲከፍሉ  መጠየቃቸው እንዳበሳጫቸው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ነጋዴዎች ለመንግስት አቤቱታ እያቀረቡ ቢሆንም፣ ከመስተዳድሩ በኩል ይህ ነው

የሚባል መልስ አላገኙም። በሌላ ዜና ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ መስሪያ ቤቶች በጀት አጠቃቀምና አያያዝ ካለፈው ዓመት መሻሻል ያልታየበትና ለልዩ ኦዲት ሪፖርቶች ምላሽ የመስጠት ዝግጁነት ዝቅተኛና አዝጋሚ ሆኖ መታየቱን የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣5ኛዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባህርዳር ከተማ ባካሄደበት የመጀመሪያ ቀን ውሎው በቀረበው የኦዲት ሪፖርት 31 መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች  በኦዲት ምርመራ ጊዜ በታየባቸው ጉድለት ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠየቁም በዓመቱ ውስጥ ምንም ምላሽ

አለመስጠታቸውን የኦዲት ቢሮው ሃላፊ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ዋና ኦዲተር ደሴ ጥላሁን ባቀረቡት በዚህ ሪፖርት በ2005/2006 የበጀት ዓመት ኦዲት ከሆኑት 152 መስሪያ ቤቶች ውስጥ የገንዘብ አያያዝና አስተዳደሩም ሆነ የውስጥ ቁጥጥር ሥርአቱን መርምሮ ተዓማኒነቱንና በቂ የሂሳብ አያያዝ

አስተዳደር መኖሩን ለማረጋገጥ ስለ ሂሳቡ ትክክለኛ መሆን አለመሆን ሙያዊ አስተያየት ለመስጠት አለመቻሉ ጉልህና መሰረታዊ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡በኦዲት ህጉ መሰረት በአግባቡ ያልሰሩ ስድስት መስሪያ ቤቶች መካከል የወልዲያና ቦሩ ሜዳ ሆስፒታሎች እንዲሁም የአንዳስ ዶሮ ብዜት ማዕከልም

በችግር ውስጥ መሆናቸው በኦዲቱ ሪፖርት እንደታየ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዋና ኦዲተሩ አባባል -በተጠቀሰው የበጀት ዓመት ሂሳባቸው ኦዲት ከተደረጉት መካከል የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ከወጪ ቀሪ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ያልተቻለባቸው 59 መስሪያ ቤቶች ችግር አለባቸው፡፡

ኦዲት ከተደረጉ  ሶስት መስሪያ ቤቶች ከ 84 ሽህ ብር በላይ በገንዘብ ያዦች የባከነና በመስሪያ ቤቶች የገንዘብ ካዝና ሰኔ 30 መገኘት ከነበረበት ገንዘብ በ 9 መስሪያ ቤቶች 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር  በጉድለት መገኘቱ ሌላው በምዝበራው ዙሪያ የተጠቀሰው የሪፖርቱ አካል እንደ ሆነ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የማጭበርበር ድርጊት ተፈጸመበት ጉዳይና ዘዴዎቹ ሲሆኑ ከህዝብና መንግስት የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት አላማ ሳይውል በፎገራ ፣ደሴ ዙሪያና ጓንጓ ወረዳዎች በሶስት መስሪያ ቤቶች ከ86 ሽህ ብር በላይ ለብክነት እንደተዳረገ  ተናግረዋል፡፡

በበጀት አመቱ መሰብሰብ ከነበረበት ገንዘብ ውስጥ ሳይሰበሰብ የቀረ በውዝፍ የሚገኝ በ48 መስሪያ ቤቶች 26.1 ሚሊዮን ብር በገቢ አሰባሰብ ስርዓት መሰረት ገቢ አለመደረጉም ተገልጿል፡፡

ያለ አግባብ በተፈጸመ ክፍያ ዙሪያም የክልሉ 106 መስሪያ ቤቶች  ወይም ኦዲት ከተደረጉት 70 በመቶ ያህሉ ክፍያዎችን በፋይናንስ ደንብና መመሪያ መሰረት ባለመፈጸም ከ 8.6 ሚሊዮን ብር በላይ መባከኑን በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ በሚሰሩ ልዩልዩ የግንባታ ስራዎች የሚሰራውን ብክነትም ሲናገሩ በ27 መሰሪያ ቤቶች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ከተያዘው የግንባታ ውል ጋር ባልተጣጣመ ሁኔታ ክፍያ በመፈጸም የህዝብ ንብረት ለብክነት ተዳርጓል፡፡

በክልሉ አዲት በተደረጉት መስሪያ ቤቶች አስራ ሁለቱ ላወጡት ወጪ ክፍያ የፈጸሙባቸውን ማስረጃ ተጠይቀው ባለማቅረባቸው 13.8 ሚሊዮን ብር በጉድለት ተገኝቶባቸዋል፡፡

በግዢ ስርአት ዙሪያም መመሪያውን የልተከተለ ግዢ የፈጸሙ 118 መስሪያ ቤቶች ከ107.3 ሚሊዮን ብር በላይ ለብክነት መዳረጋቸውን ገልጸው፤ካለፈው አመት ሪፖርት በመነሳት የግዢ መመሪያውን በመፈጸም ላይ አሁንም መሻሻል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ ባሉ መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የሆነ ለምዝበራ የሚጋልጡ የአሰራር ግድፈቶች መኖራቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው፤ ገቢ ተሰብሰቦባቸው ለኦዲት ያልቀረቡ ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ የያዙ ደረሰኞች በየወረዳዎቹ በተለያዩ ሃላፊነት የሚገኙ ተሿሚዎች የተመዘበሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለሰራተኛ ከሚከፈል ደመወዝ በላይ በጀት እንዲጸድቅ በማድረግ ልዩነቱን ለግል ጠቅም ማዋል ፣በአንድ አመት የ567 ቀናት ውሎ አበል መወሰድ ፣ከዕቃ አቅራቢዎች ጋር በመመሳጠር የማጭበርበር እና ኢፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ማድረግ ፣ የግንባታ ጥራት ላልጠበቁ ስራዎች ክፍያ ከፍለው መገኘት ፣ መስክ

የወጡ በማስመሰል የመኪና ነዳጅ ቅባትና ጥገና ገንዘብ በማውጣት ለግል ጥቅማቸው ማዋል በሹማምንቱ ከተሰሩት ወንጀሎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን  በሪፖርታቸው ማጠቃለያ አቅርበዋል፡፡

በአንድ በኩል መንግስት ህዝቡን እያጨናነቀ ግብር እንዲከፍል ሲያደርግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከድሃው የሚሰበሰበውን ገቢ ባለስልጣናቱ በየጊዜው መዝረፋቸው ነጋዴዎችን እያበሳጨ መሆኑን የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጻለች።