ታህሳስ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ በጉንዶመስቀል ከተማ በመስተዳድሩ ውስጥ ተቀጥረው ከሚሰሩት መካከል ከ108 በላይ ሰዎች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች የተለያዩ የሃለፊነት ቦታዎችን ወስደዋል በሚል የአካባቢው ፖሊስ ምርመራ በማድረግ ላይ ነው።
ፖሊስ እስካሁን ባደረገው ምርመራ 13 ሰዎች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው ለአመታት ደሞዝ ሲቀበሉ መቆየታቸውን በማረጋገጥ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መርቶታል። በቀሪዎቹ ላይ ምርመራ በማድረግ ላይ እያለ አስተዳዳሪው ምርመራው እንዲቋረጥ ትእዛዝ ሰጥተዋል። አስተዳዳሪው ” አካሄዱ ልማት የሚያደናቅፍ” የሚል ምክንያት የሰጡ ሲሆን፣ ፖሊስና ፍርድቤቱ ግን የአስተዳዳሪውን ምክንያት ባለመቀበል ምርመራውን በማካሄድ ላይ ናቸው።
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሀላፊነት ቦታዎችን ከያዙት መካከል የዋና አስተዳዳሪው ታናሽ ወንድም አንዱ ሲሆን፣ አስተዳዳሪው ምርመራው እንዲቋረጥ ያስደረጉት ከዚህ የተነሳ መሆኑን ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ሃለፊ፣ የትራንስፖርት ዘርፍ ሃላፊ እንዲሁም የአስተዳዳሪው ወንድም የሆኑት የውሀ አገልግሎት ሃላፊ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው መስራታቸው ከተረጋገጠባቸው መካከል ይገኙበታል።
ፖሊስ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው 13 ሰዎች በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል።