የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ከስልጣን ተነሱ

(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-የአማራ ክልልን ላለፉት ስምንት ዓመታት ተኩል በፕሬዚደንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አያሌው ጎበዜ ከኃላፊነታቸው ተነሱ፤ በምትካቸው ምክትል ፕሬዚደንቱ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተሹመዋል፡፡

አቶ አያሌው ከኃላፊነታቸው የተነሱት እየተካሄደ ባለው የአማራ ክልል ምክር ቤት አራተኛ ዙር ፤ አራተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ነው፡፡

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በአቶ አያሌው መውረድና በአቶ አንዳርጋቸው መተካት ዙሪያ የብአዴን አባላት ሙሉ ስምምነት ላይ አልደረሱም። አዲሱ ፕሬዚዳንት በሙስና የተዘፈቁ እና በዘመድ አዝማድ ስራዎች የሚታወቁ በመሆኑ፣ በርካታ የብአዴን አባላት ሹመቱን አልደገፉትም።

ያለፈውን አንድ ወር በባህርዳር እና ጎንደር በመመላለስ ያሳለፉት አቶ በረከት ስምኦን ከክልሉ ብአዴን ካድሬዎች ጋር ግምገማዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ካሉት የብአዴን አመራሮች መካከል በአንጻራዊ መልኩ የተሻለ ስም የነበራቸውን አቶ አያሌው ጎበዜን በማንሳት እንደ አቶ በረከት ሁሉ የተበላሸ ስም ያላቸውን አቶ ገዱን ለመተካት የተፈለገበት ጉዳይ ብዙ ውስብስብ ጉዳዮችን ያዘለ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።