በጉራፈርዳ ወረዳ ተጨማሪ የአማራ ተወላጆች ተፈናቀሉ

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አዲሱ ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ ባለስልጣኖቻቸው ከእንግዲህ አንድም ሰው እንዳያፈናቅሉ ባስጠነቀቁ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ የሚኖሩ 90 የአማራ ተወላጅ አባዎራዎች ከክልሉ መባረራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

እንደገለጹት የአማራ ተወላጆች በተቀነባበረ ዘመቻ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ ነው። እስካሁን የተባረሩት ሰዎች አድራሻቸው ካለመታወቁም ሌላ ፣ ባለፉት ሁለት ቀናት የተባረሩ ቤተሰቦችም የት እንደደረሱ አይታወቅም። አርሶ አደሩ እንደሚሉት በተራቀቀ ዘዴ የአማራ ተወላጆችን ከክልሉ ማስወጣቱ ይቀጥላል።

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር ከእንግዲህ የትኛውም ባለስልጣን ሰዎችን ቢያፈናቅል ተጠያቂ ይሆናል ብለው ማለታቸው ይታወሳል።

የአማራ ተወላጆችን ከሌሎች ክልሎች የማስወጣቱ ድረጊት በዘር ማጥራት ወንጀል እንደሚያስጠይቅ እውቁ የአለማቀፍ ህግ ባለሙያ ዶ/ር ያእቆብ ሀይለማርያም መናገራቸው ይታወሳል።