ለኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች ከፍተኛ ጥቅማጥቅም የሚሰጥ አዋጅ ተረቀቀ

ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች ስራቸውን አጠናቀው ወደአገር ውስጥ ሲመለሱ ከቀረጥ ነጻ ዕቃዎቻቸውን ማስገባትን ጨምሮ
ከፍተኛ የደመወዝ ክፍያና ጥቅማጥቅም የሚያስገኝ አዋጅ ተረቀቀ፡፡
በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረቅቆ በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቆ ሰሞኑን ለፓርላማው የቀረበው የውጪ ግንኙነት አገልግሎት
ረቂቅ አዋጅ ክፍል ስድስት ከ37 እስከ 41 ያሉት አንቀጾች የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ሰራተኞችን ልዩ ልዩ
ጥቅማጥቅምና ከለላዎችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን የያዙ ናቸው፡፡

እስካሁን ሲሰራበት የቆየውን ልማዳዊ አሰራር ያስቀራል የተባለው ይህው አዋጅ የዲፕሎማቲክ ሚስዮን መሪ ወይም ቋሚ መልዕክተኛ በተሟላ እና ሙሉ ወጪው በመንግስት በሚሸፈን ቤት ውስጥ እንደሚኖር፣የመኖሪያ ቤት ድጋፍ አገልግሎት በመንግስት ወጪ
እንደሚቀጠሩለት፣ደረጃውን የጠበቀ መኪና ከነአሸከርካሪው እንደሚመደብለት ያትታል፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ሰራተኛ በሚስዮኑ ቆይታው ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የደመወዝ
ክፍያ ከግኘቱም በተጨማሪ ግብር የማይከፈልበት አበል እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
የውጪ ግንኙነት አገልግሎት ሰራተኛው የሚስዮን ቆይታውን አጠናቆ ወደሚኒስቴሩ በሚመለሰበት ግዜ ለግል አገልግሎቱ
የሚጠቀምበትን አንድ መኪናና የግል መገልገያ ዕቃዎቹን ከማናቸውም ቀረጥና ታክስ ነፃ ማስገባት እንደሚችል
ተደንግጓል፡፡ይህ አሰራር ቀደም ሲልም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በወጡ
መመሪያዎች ይሰራበት እንደነበር ሰነዱ ይጠቁማል፡፡
በተጨማሪም በውጪ ግንኙነት ሰራተኛው በስራ ላይ እያለ ከሞተ ለቤተሰቡ የሶስት ወራት ደመወዝ፣የኑሮ መደጎሚያና
የቤት ኪራይ አበል ይከፍላል፡፡ የጤና መድን ዋስትናውንም ይሸፍናል ይላል፡፡በሚስዮን ተመድቦ የሚሰራ ሰራተኛ
የቤተሰቡ አባል ከሞተ አስከሬኑን ወደአገር ቤት ለማጓጓዝና አስከሬኑን አጅበው ለሚጓዙ የቤተሰብ አባላት
የሚያስፈልገውን ወጪ ሚኒስቴሩ እንደሚሸፍን በረቅቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡
በተጨማሪም የአምባሳደርነት ማዕረግ የአገልግሎት ጊዜ ካበቃም በኋላ የዕድሜ ልክ መጠሪያ ሆኖ እንዲቆይ ሚኒስቴሩ
ወደፊት በመመሪያ እንዲያወጣ አዋጁ ደንግጓል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በስራ ላይ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ሜሪትን ሳይሆን የፖለቲካ አቋማቸው ብቻ እየታየ የሚሾሙ በመሆናቸው
አገሪቱ ከውጪ ግንኙነት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያስገኙ አለመሆኑ በየጊዜው ትችት የሚቀርብበት መሆኑ የሚታወቅ
ነው፡፡ በርካታ ዲፕሎማቶች አገልግሎታቸውን ከጨረሱ በሁዋላ ወደ አገር ቤት አይመለሱም። የተሻለ እውቀት ያላቸው ዲፕሎማቶች ከኢኮኖሚው ችግር በተጨማሪ በሙያው ምንም ልምድ የሌላቸው በአብዛኛው የህወሀት ነባር ታጋዮች በሚሰጡዋቸው ትእዛዝ እንደሚማረሩና ስራቸውን እንደሚለቁ መዘገቡ ይታወሳል።