የኔዘርላንዷ ንግስት ስልጣናቸውን ለልጃቸው አስረከቡ

ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ላለፉት 33 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የኔዘርላንድስ ንግስት ቢያትሪክስ በአምስተርዳም  እጅግ በደመቀ ስነስርአት ስልጣናቸውን ለ46 አመቱ ልጃቸው ዊሊያም አሌክሳንደር በየአመቱ ሚያዚያ 30 በሚከበረው የንግስቷ የልደት ቀን በአል ላይ አስረክበዋል። የንጉሱ ባለቤት የሆኑት አርጀንቲናዊዋ የባንክ ሰራተኛም በስነስነስርአቱ ላይ ንግስት ተብለው ተሹመዋል።

በኔዘርላንድስ የነገስታቱ ባህል መሰረት በስልጣን ላይ ያለው ንጉስ ወይም ንግስት እድሜያቸው ሲገፋ ስልጣናቸውን ያስረክባሉ። ስልጣኑን ከናታቸው የተረከቡት ንጉስ ዊሊያም ለህዝቦች መቀራረብ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። በኔዘርላንድስ ነገስታቱ ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ባይኖራቸውም ለአገሪቱ አንድነት አስፈላጊ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ ክብር አላቸው።

ከ 123 አመታት በሁዋላ በኔዘርላንድስ ንጉስ ሲሾም ዊሊያም አሌክሳንደር የመጀመሪያው ነው።  በስልጣን ተዋረዱ መሰረት የ9 አመቷ የኦሬንጇ ልእልት ካተሪና አማሊያ  ተተኪዋ ንግስት ተብላለች።