በገጠር መንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ በብልሹ አሰራር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየባከነ ነው

ታህሳስ ፳፩ ( ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በባለስልጣኑ ውስጥ በብልሹ አሰራር   በትግራይ ክልል 37 ሚልየን 832 ሺ 770 ብር 35 ሳንቲም ለብክነት ተዳርጓል፡፡

በኦሮምያ ክልል ከ17 ሚልየን 892 ሺ ብር በላይ ፤ በደቡብ ክልል ከ23 ሚልየን 19 ሺ ሰባ ሶስት  ብር አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ባክኗል።

በመተማ አብረሃጅራ ፕሮጀክት ብቻ  16 የኪራይ ገልባጭ መኪኖች 24 የተለያየ መጠን ያላቸዉ ብዛታቸዉ 369 ጎማዎች ዉስጥ 54ቱ አገልግልት የማይሰጡ፣ ቀሪዎች 315 ደግሞ መስራት እየቻሉ ያለ አገልግሎት የተቀመጡ ፣ በጥገና ጽ/ቤቱ ያለስራ ተከማችተው የሚገኙ  1 ሚሊዮን154 ሺ 831 ብር ከ33 ሳንቲም ዋጋ የሚያወጡ ብዛታቸው 9 ሺ 046 እና ዋጋቸው የማይታወቅ ብዛታቸው 1 ሺ 077 የሆነ የተለያዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች የተከማቹ ሲሆኑ፣ 3 የማይሰሩ ሞተር ሳይክሎች፣1 የማይሰራ መበየጃ ማሽን፣ 2 ሚክሰሮች በሞተር ችግር ምክንያት፣1 የማይሰራ የቅየሳ መሳሪያና እንዲሁም 2 የማይሰሩ ጀኔሬተሮች ያለምንም እርምጃ ተቀምጠው የሚገኙ መሆኑ ተመልክቷል።

በፕሮጀክት ጽ/ቤት ከቆሙ 11 መሳሪያዎች ላይ ከብር 36 ሺ 950.00 ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ዕቃዎች መጥፋታቸው፣ በፕሮጀክት የነበረች የሰሌዳ ቁጥር 4-03065 ቶዮታ ዳብል ጋቢና መኪና እንዲያሽከረክር ኃላፊነት ባልተሰጠው አካል  በደረሰባት የመገልበጥ አደጋ ለጥገና ብር 346 ሺ 627 ወጪ ሁኗል፡፡

የችግሮቹ መከሰት ዋና ዋናዎቹ መንስኤዎች ባለስልጣን መ/ቤቱም ሆነ በስሩ የሚገኙት ጥገና ጽ/ቤቶችና ፕሮጀክቶች በመለዋወጫዎች ቁጥጥር፣ አያያዝና አጠባበቅ ዘሪያ የተሟላ፣ ግልፅና ዘመናዊ የሆነ የአስተዳደር ስርአት ካለመዘርጋታቸውም በላይ የህዝብን  የንብረት አያያዝና አስተዳደር መመሪያን ተከትሎ አለመስራት፣ ግዥን አስቀድሞ በትክክል ካለ ማቀድና ተገቢ ጥንቃቄ አለማድረግ፣የንብረት አወጋገድ ስርዓትን ተከትሎ አለመስራት፣ለሚከሰቱ ችግሮች ወቅታዊ ምላሽ አለመስጠት እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ጉዳዩች የሚመለከታቸው አካላት ቸልተኝነት በመኖሩና የተጠያቂነት ስርዓቱ በመላላቱ ነው ተብሎአል።

በዚህም ባለስልጣን መ/ቤቱ የተገለጹት ችግሮች መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ በማስተካከል የተጣለበትን ሃላፊነት መወጣት የሚያስችለውን አሠራር መዘርጋትና የተመደበለትን ውስን ሃብት በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል አልቻለም ተብሎአል።