የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን ከደቡብ ሱዳን ማስወጣት መጀመሩን አስታወቀ

ታህሳስ ፳፩ ( ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ 1 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከቦርና ቢንቲዩ ግዛት መውጣታቸውን እና 650 የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ቀሪዎቹ ደግሞ ዋና ከተማዋ ጁባ መግባታቸውን ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ እንዳሉት ሁኔታዎች እየከፉ የሚሄዱ ከሆነ ቀሪዎቹን ዜጎች የማውጣት እቅድ አለ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በግጭቱ ውስጥ ከሞቱት 1 ሺ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበትም አስታውቋል። እስካሁን ምን ያክል ኢትዮጵያን በትክክል እንደሞቱ አልታወቀም፡ የኢትዮጵያ መንግስትም መረጃውን ይፋ አላደረገም፣ ይሁን እንጅ የአሜሪካ ድምጽ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በመጥቀስ ከ30 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን እንደሞቱ ዘግቧል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በደቡብ ሱዳን ከ15 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ገልጿል። ይሁን እንጅ አንዳንድ ወገኖች ቁጥሩ 50 ሺ ይደርሳል ይላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኡጋንዳው መሪ ዪዎሪ ሙሰቨኒ ለአማጽያኑ መሪ ሪክ ማቻር ፣ “የሰላም ስምምነቱን የማትቀበል ከሆነ ሽንፈት ይጠብቅሃል” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ልከዋል። ዩጋንዳም ጦሯን ወደ ሱዳን ማስገባቱዋን በይፋ አስታውቃለች።

የዩጋንዳ  መንግስት ያዘው አቋም በደቡብ ሱዳን የተጀመረውን የሰላም ጥረት እንደሚያበላሸው አማጽያን አስጠንቅቀዋል።