ለስኳር ፕሮጀክቶች ገንዘብ አልተገኘም ተባለ

ታህሳስ ፳፩ ( ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሪፖርትር እንደዘገበው በአምስት አመቱ የልማት እቅድ መሰረት 10 አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለመገንባትና 3 ነባር ፋብሪካዎችን ለማስፋፋት እንዲሁም የተጓተተውን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ለማጠናቀቅ እቅድ ቢወጣም ፣ ሶስቱ ነባር ፋብሪካዎች ከህንድ በተገኘ 640 ሚሊዮን ዶላር ብድር ግንባታቸው እየተካሄደ ሲሆን፣ ለአዳዲሶቹ በቂ ገንዘብ አልተገኘም። የስኳር ኮርፖሬሽኑ 75 ቢሊዮን ብር ከመንግስት ግምጃ ቤት በሚገኝ ፋይናንስ ለመገንባት አቅዶ ነበር። ይሁን እንጅ የተገመተውን ገንዘብ ያክል ለማግኘት ባለመቻሉ መንግስት ግንባታውን በሽርክና እንዲካሄድ መመሪያ ለመስጠት መገደዱ ተዘግቧል።

የአምስት አመቱ የልማት እቅድ ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜ አንድ አመት ብቻ ነው። በሟቹ ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ተዘጋጅቶ የቀረበው የአምስት አመቱ የልማት እቅድ በገንዘብ አቅርቦት ችግር ምክንያት እንደማይሳካ ምሁራን ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወቃል። አሁን በሚታየው ሁኔታ የእቅዱ ግማሽ ያክል እንኳ መሳካቱ አጠራጠሪ ሆኗል። መንግስት በአምስት አመታት ውስጥ 14 በመቶ አማካኝ እድገት ለማግኘት ቢያቅድም እስካሁን የተገኘው እድገት ከ7 እስከ 8 በመቶ እንደማይበልጥ ያሳያል።