በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የታሰበው የዕርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠ

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)

ኢትዮጵያውያን የድርቅ ተጠቂዎችን ለመታደግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ (OCHA) ከሌሎች ለጋሾች ጋር ያስተባበረው የዕርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠ። የኢሳት ምንጮች ከአዲስ አበባ እንደገለጹት ለአዲስ አበባው የኦቻ (OCHA) ተጠሪ ማሰባሰቢያውን የሰጡት የጠ/ሚኒስትሩ ልዩ መልዕከተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ናቸው።

10.2 ሚሊዮን በቀጥታ በድርቁ ተጠቂ በመሆናቸው ሌሎች 8 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በሶፍትኔት የታቀፉ የዕለት ድረሽ ምግብ ጠባቂ በመሆናቸው ለ18 ሚሊዮን ህዝብ ምግብ በማስፈለጉ ዓለም-አቀፍ ድርጅቶቹ እ/ኤ/አ ማርች 23/2016 የዕርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውም ታውቋል።

ይህ በመገናኛ ብዙሃን የተጀመረው የዕርዳታ ዘመቻ የኢትዮጵያን ገጽታ ይጎዳል በሚል መንግስት እንደቆይ መወሰኑን መረዳት ተችሏል።

ከ10 ቀናት በፊት እ/ኤ/አ ማርች 23/2016 ለኢትዮጵያውያን ዕርዳታ ለማሰባሰብ በፌስ ቡክ፣ ትዊተር እና በለጋሾች ዌብሳይት ዘመቻውን የጀመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነው የሰብዓዊ ጉዳዮችን ቢሮ (OCHA) የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት ዩ ኤስ ኤይድ (USAID) ሴቭ ዘ ችልድረን (SAVe The Childeren)፣ ዩኒሴፍ (UNICEF)፣ እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

በተያዘው የምዕራብያውያኑ ዓመት 2016 ረሃብተኛ ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ የሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ባለመገኘቱ አለም-አቀፍ ተቋማቱ ዘመቻውን ከፍተዋል።

የጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ልዩ መልዕክተኛ የሚል ሹመት የተሰጣቸው የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ዘመቻው እንዲቆም አሳስበው ዕርዳታውን እንዳይሰባሰብ ለኦቻ (OCHA) ዳይሬክተር መናገራቸውን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኦቻ (OCHA) ዳይሬከተር በበኩላቸው ለጋሾቹ ወደ ሚዲያ ዘመቻ ለመግባት የተገደዱበትን ሁኔታ አስረድተዋል። የድርቅ ተጎጂዎች ለመታደግ የሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የተገኘው ከግማሽ በታች 686 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ በአለም-አቀፍ ለጋሾች በኩል የታየውን ደካማ ምላሽ ለማሸነፍ ሲባል ዘመቻው መከፈቱን አብራርተዋል።

አምባሳደሩ የመንግስታቸው አቋም የማይቀየርና ዘመቻው መሰረዙ የግድ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ዕርምጃው የኢትዮጵያን መንግስት ገጽታ በአለም-አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል በማለት ማሳሰባቸውም ተመልክቷል። በተጨማሪም ለገንዘብ ዕጥረቱ ለየትኛውም የምዕራብ ሚዲያ እንዳይሰጡም ማሳሰባቢያ ተሰጥቷቸዋል።

በኢትዮጵያ የኦቻ ተወካይ ከአምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ማሳሰቢያ በኋላ፣ አለም አቀፍ ደረጃ ያለው ምላሽ ደካማ መሆኑን በመግለፅ፣ ዘመቻውን ለመክፈት የተገደደበትን ሁኔታ ያስረዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አለ ያሉትንም አሳሳቢ ችግር ጠቅሰዋል።

በሶማሊ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ክልል ላለፉት 60 ቀናት ድጋፍ ያላገኙ ተረጂዎች መኖራቸውን የጠቀሱ ስሆን፣ አምባሳደር በቂ ምግብ ወደብ ላይ አለ፣ ችግሩ ትራስፖርት ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሰለባዎቹ ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ በሚመለከት፣ መንግስት ውሳኔውን እንደገና እንዲመረምር መማጸናቸውም ተመልክቷል። ሆኖም አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ  የመንግስት ውሳኔ የማይለወጥ መሆኑን አስረግጠው ካልተስማማችሁ ቢሯችሁን ዘግታችሁ መውጣት ትችላላችሁ ሲሉ ማሳሰባቸውን ለኢሳት በዝርዘር የደረሰው መረጃ ያሳያል።

10.2 ሚልዮን የድርቅ ተጠቂዎችን እንዲሁም በሶፍት ኔት የታቀፉ 8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ 18.2 ሚሊዮን ዜጎች ለመታደግ ማርች 23/2016 የተጀመረው ዘመቻ የመንግስትን ማሳሰብያ ተከትሎ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተቋርጧል። ዘመቻው የተከፈተው ለ90 ቀናት እንደነበርም ታውቋል።