ለህዳሴ ግድብ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተጠሩ ስብሰባዎች በተቃውሞ ተበተኑ

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)

ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ ለማሰባሰብና ለኮንዶሚኒየም በሚል በአሜሪካና በአውሮፓ ከተሞች የተንቀሳቀሰው የመንግስት ተወካዮች ተቃውሞ ቀረበባቸው። ስብሰባዎችም በተቃውሞ ተበተኑ።

በአሜሪካ ፔንስልቬንያ ግዛት የፊላዴልፊያ ከተማ እንዲሁም በጣሊያን ቱርኒ በሳምንቱ መጨረሻ የተጠሩት ስብሰባዎች ያለውጤት በተቃውሞ መበተናቸውን ለኢሳት በቪድዮ የደረሰው ዜና ያስረዳል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ርሃብ እንዲሁም በኦሮሚያ የቀጠለውን ግድያና እስራት እያነሱ ተቃውሞ ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን፣ የአንድ ብሄር የበላይነት በሃገሪቱ አለ ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል። በአሜሪካ ፊላዴልፊያ፣ በጣሊያ ቱሪን በሳምንቱ መጨረሻ የተቃውሞ ቪዲዮች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ሲሰራጩ ቆይተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በጀርመን ፍራንክፈርት “የዳያስፖራ ቀን” በሚል ብዓዴን የጠራውን ስብሰባ በመቃወም ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።