የጋዜጠኛና ደራሲ ሙሉጌታ ሉሌ የመታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)

የአንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ሃያሲ፣ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ የመታሰቢያ ፕሮግራም ባሳለፍነው ቅዳሜ ሚያዚያ 1 ቀን 2008 ዓም በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ዋለ።

አዘጋጅ ኮሚቴው እንደገለጸው ከሆነ ሙሉጌታ ሉሌ በህይወት ዘመኑ ለሃገርና ለህዝብ ላበረከተው አስተዋፅዖ ለማመስገንና ህያው ስራዎቹ ለመዘከር በማሰብ የተዘጋጀ ፕሮግራም ሲሆን፣ ዝግጅቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ስኬታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁ ለኢሳት ገልጸዋል።

የጋዜጠኛና ደራሲ ሙሉጌታ ሉሌ የአክብሮት ቀን ሃውልት ምረቃ፣ ማዕዛ ሬስቶራንት በተካሄደ የመታሰቢያ ፕሮግራም መካሄዱንም ታውቋል።

በአርሊንግተን መካነ መቃብር በተካሄደው የሃውልት ምርቃት የሙሉጌታ ሉሌ ቤተሰቦች፣ የቅርብ ጓደኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን፣  ፕሮግራሙ በጸሎት፣ በመዝሙርና መንፈሳዊ መልዕክት እንዲታጀብ ተደርጓል።

በማዕዛ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት በተካሄደው የምሳ ፕሮግራም በአዘጋጅ ኮሚቴው ግብዣ የተደረገላቸው የሙሉጌታ ሉሌ ቤተሰቦች ጓደኞች እና የስራ ባልደርቦች ንግግር አድርገዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በአርሊንግተን ማርየት ሆቴል በተካሄደው የአክብሮት እና ምስጋና ፕሮግራም የሙሉጌታ ሉሌ ቤተሰቦችና የቅርብ ወዳጆች ስለ አንጋፋው ጋዜጠና ሃገራዊ ፍቅር፣ የመብትና የፍትህ አርበኝነት፣ የእኩልነት እና ዲሞክራሲ አቀንቃኝነት በማንሳት ክብራቸውን ገልጸዋል። የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሃይል ማህበርም የማህበራቸው የክብር አባል ለሆነው ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በመያዝና በሰልፉ አዳራሽ በመግባት የክብር ሰላምታ አቅርበዋል።

በዝግጅቱ ላይ የጋዜጠኛ እና ደራሲ ሙሉጌታ ሉሌን የሚዘክር መጽሄት እና ዘጋቢ ፊልም የቀረበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን በአንጋፋ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ስም የተዘጋጀ የማስታወሻ ላይብራሪ ይፋ አድርጓል።