ታህሳስ 03 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልል በምእራብ ጎጃም ዞን በዳንግላ ወረዳ ነዋሪ የሆነው መምህር ምህረት በደህንነት ሀይሎች ታፍኖ የተወሰደው ከሳምንት በፊት ነው።
የኢሳት የአማራ ክልል ዘጋቢ እንደገለጠው ማንነታቸው ያልታወቁ ራሳቸውን የደህንነት ሰራተኞች አድርገው ያስተዋወቁ ሲቪል የለበሱ ሰዎች መምህሩን ከክፍል አስወጥተው ወደ አልታወቀ ስፍራ ወስደውታል።
መምህሩ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የማእከላዊ እስር ቤት ሳይወሰድ እንዳልቀረ ግምቶች መኖራቸውንም ገልጧል።
በክልሉ መንግስትን የሚቃወሙ ሀይሎች ሁሉ የግንቦት7 አባል ናችሁ እየተባሉ ታፍነው እየተወሰዱ ነው።
በምእራብ ጎጃም ዞን ይኖሩ የነበሩ 4 ወጣቶች የግንቦት 7 የእቡዕ አባል ናቸው ተብለው በመጠርጠራቸው በደህንነት ሰዎች ተወስደው መታሰራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ወጣቶቹ የተያዙት ኖቬምበር 7፣ 2011 ወይም ጥቅምት 30፣ 2004 ሲሆን፣ ከአንደኛው ወጣት አድርሻ በስተቀር ሶስቱ ወጣቶች ያሉበት ቦታ እስካሁን አልታወቀም።
አያልሰው የተባለው ወጣት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስሮ ሲገኝ በሽብር ወንጀል የሚፈለገው ሙሉጌታ የኔአለም የተባለው ወጣት ደግሞ ጓደኞቹ በተያዙበት እለት በአካባቢው ባለመኖሩ ሳይያዝ መቅረቱንና አሁንም እየታደነ እንደሚገኝ ቤተሰቦቹን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል።
የመለስ መንግስት ለስልጣኔ ያሰጋሉ ያላቸውን ሀይሎች ሁሉ በሽብርተኝነት ስም እያሰረ እንደሚገኝ ይተወቃል።