ሱዳንና ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት ተቃዋሚዎችን በየአገሮቻቸው ላለማስተናገድና አሳልፎ ለመስጠትም ተስማሙ

03 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው አገራቱ በየአገሮቻቸው ያሉ አማጽያንን ለማስወጣትና አሳልፎ ለመስጠት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የሁለቱ አገራት የድንበር ጉዳይ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ የተገኙት የሲናር ክፍለሀገር ገዢ የሆኑት አህመድ አባስ ፣ ሁለቱ አገሮች በድንበር አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አማጽያንን አሳልፈው ለመስጠት መስማማታቸውን አረጋግጠዋል።

የመለስ መንግስት የሱዳንን መንግስት ላለማበሳጨት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን የዘገበው ሱዳን ትሪቢዩን፣ በቅርቡ የሱዳን አማጽያንን ከኢትዮጵያ የድንበር ከተሞች ማስወጣቱን በምሳሌነት አንስቷል።

የሱዳን መንግስት ላለፉት 20 አመታት የኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር እና የሌሎችንም የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ድርጅት  አባላትን  ለመለስ መንግስት አሳልፎ ሲሰጥ ቆይቷል።

በአጸፋውም የመለስ መንግስት  የቤልጂየምን አጠቃላይ ግዛት የሚያክል 30 ኪሎሜትር ስፋትና 1 ሺ ኪሎሜትር ርዝመት ያለው  መሬት ለሱዳን መንግስት አስረክቧል።

ዊኪሊክስ የመረጃ ማእከል አቶ መለስ ዜናዊ የሱዳኑ መሪ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን እንዲወገዱ ለአሜሪካኖች ምክር መስጠታቸውን ይፋ ቢያደርግም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሁለቱን መንግስታት ህልውና የሚወስን መሆኑን በመረዳት የእከክልኝ ልከክልህ ፖሊሲ ማራመድን መርጠዋል ሲል የኢሳት የጥናት ቡድን አስተያየቱን አስፍሯል።