በደብል ትሪ ሆቴል ላይ የተጀመረ ምርመራ የለም ተባለ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 5/2010) ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባው ደብል ትሪ ሆቴል ንብረታቸው ላይ የተጀመረ ምርመራ የለም ሲሉ አቶ ተካ አስፋው ለኢሳት ገለጹ።

የሆቴሉን ግንባታ ያካሄዱት ሼህ መሀመድ አላሙዲን ባደረጉላቸው ድጋፍና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወሰዱት ብድር መሆኑንም ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደርኩት ገንዘብ 300 ሚሊየን ተብሎ የተጠቀሰውም ስህተት ነው ሲሉ አቶ ተካ አስፋው ተናግረዋል።

ኢሳት ምንጮችን በመጥቀስ ባቀረበው ሁለት ተከታታይ ዘገባ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው ደብል ትሪ ሆቴል ንብረትነቱ በአቶ ተካ አስፋውና ቤተሰባቸው የተመዘገበ ነው።

ነገር ግን ሆቴሉ የአቶ በረከት ነው በሚል በመንግስት የጸጥታ አካላት ምርመራ መጀመሩን ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።

ሆቴሉ 300 ሚሊየን ብር እንደፈጀና ይህም ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደ ብድር መሰራቱን በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሆነም ኢሳት ምንጮችን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።

በኢሳት የቀረበውን ዘገባ በሆቴሉ ባለንብረትነት የተመዘገቡት አቶ ተካ አስፋው ርሳቸው በሚያውቁት ደረጃ የሚካሄድ ምርመራ አለመኖሩን ገልጸዋል።

አቶ በረከት ስምኦን በረሃ ሳይወጡ የአንድ አካባቢ ሰዎች ከመሆናቸው ውጭ ከርሳቸው ጋር የሚያገናኛቸው ነገር አለመኖሩንም ተናግረዋል።

የሆቴሉን ግንባታ በተመለከተ በሼህ መሀመድ አላሙዲን ድጋፍና በራሳቸው ጥረት የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሼህ መሀመድ አላሙዲን ወደ 60 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የዳሽን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በመሆኔ ከዚያ ብድር መውሰድ የምችል ቢሆንም የጥቅም ግጭት ያስነሳል በሚል ከመሬት መግዣ በተረፈኝ ገንዘብ ላይ መኪናዎቼን ሸጬ የሆቴሉን ግንባታ 40 በመቶ አጠናቅቄያለሁ።

ቀሪውንም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድሬ ግንባታውን ቀጥያለሁ ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከእሳቸው እውቅና ውጪ በሆነ መንገድ የተጀመረ ምርመራ አለመኖሩንም አመልክተዋል።

ከሼህ መሀመድ አላሙዲን ጋር ከ20 አመታት በላይ እንደሚተዋወቁና ለ12 አመታት የዘለቀ የስራ ግንኙነት እንዳላቸውም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሼህ መሀመድ አላሙዲን ኩባንያዎች ጠበቃ እንዲሁም የሼህ መሀመድ አላሙዲን የህግ አማካሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነት የተነሱትና ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ምክትል ሃላፊነታቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት አቶ በረከት ስምኦን ላይ የሙስና ምርመራ መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል።

ደብል ትሪ ሆቴል ከሚመረመሩት ተቋማት አንዱ እንደሆነም ምንጮችን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።

አቶ ተካ አስፋው እንደሚሉት እየተነገረ ያለው ሁሉ እሳቸውን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትንት ውድድር ለማሰናከል የሚደረግ ሙከራ ነው።