በኢራንና በኢራቅ ድንበር በተከሰተው ርዕደ መሬት ከ400 በላይ ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 4/2010) በኢራንና በኢራቅ ድንበር በተከሰተውና በሬክተር ስኬር 7 ነጥብ 3 በተመዘገበው ርዕደ መሬት ከ400 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ7 ሺ በላይ ሰዎች ቆሰሉ።

የመገናኛ ብዙሃን እያወጡት እንዳለው መረጃም የሟቾቹም ሆነ በአደጋው የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል።

በኢራን መንግስት ስር የሚተዳደረው ፕሬስ ቲቪ እንደዘገበውና እስከ ቱርክና ፓኪስታን ድረስ ተሰምቷል ከተባለው ርዕደ መሬት በኋላ 145 የሚሆኑና መሬትን ከሚያናውጠው አደጋ በኋላ የሚመጡ አነስተኛ መንቀጥቀጦች ተከስተዋል።

በኢራንና በኢራቅ ድንበር ላይ የተከሰተው ይህ ርዕደ መሬት ባለፈው መስከረም በሜክሲኮ ከተማ ከደረሰውና የ369 ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው አደጋ በኋላ አስከፊው አደጋ በሚል ተመዝግቧል።

በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 3 በተመዘገበው በዚህ ርዕደ መሬት ከ400 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ7 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ታውቋል።

ቢቢሲ፣ሲ ኤን ኤንና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን እያወጡት እንዳለው መረጃም ከሆነም የሟቾቹም ሆነ በአደጋው የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል።

በዚህ ርዕደ መሬት በኢራን በኮርማንሻ ግዛት በምትገኝ አንዲት ከተማ ብቻ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ሀገሪቱም ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ የሀዘን ቀን አውጃለች።

በአሜሪካ የከርሰ ምድር ጥናት መሰረት በኢራንና ኢራቅ ድንበር ላይ ማዕከሉን ያደረገው ይህ ርዕደ መሬት እስከ 23 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ሲኖረው ከዋናው መንቀጥቀጥ በኋላ የነበሩት አነስተኛ መንቀጥቀጦች ፓኪስታን፣ሊባኖስ፣ኩዌትንና ቱርክን እንደመቱ ታውቋል።

የኢራቅ የአየር ትንበያ መስሪያ ቤት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐይደር አል አባዲ ደግሞ በቲውተር መልዕክታቸው የሀገሪቱ የሲቪል ተቋማት፣የጤናና የእርዳታ ድርጅቶች የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

በተመሳሳይም የኢራኑ ታላቅ መሪ አያቶላ አሊ ከሚኒ ሐዘናቸውን በመግለጽ የወታደራዊውም ሆነ የሲቪሉ ማህበረሰብ ተጎጂዎቹ ወዳሉበት በመሄድ የበጎ አድራጎት ስራን እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

አብዮታዊ ጦር በመባል የሚታወቀው የኢራን ሰራዊትም ወደ ስፍራው መጓዙ ታውቋል።

በደቡብ ባግዳድ ነዋሪ የሆነችው ማጂዳ አሚር እንዳለችው ከሶስት ልጆቿ ጋር እራት በመብላት ላይ እያለሁ ያለሁበት ሕንጻ ድንገት በአየር ላይ ሲወዛወዝ ተሰማኝ ከዛም ሶስት ልጆቼን ይዤ ወደ መንገዱ ሮጥኩ ብላለች።

ኢራን ካላት የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ሳቢያ በአረብና በኢሲያ መካከል ባለ ስንጥቅ አካባቢ በመገኘቷ ለተደጋጋሚ ርዕደ መሬት ተጋላጭ ሆናለች።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 6 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ሀገሪቱን በመታ ጊዜ 26 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

ይህም በክፍለ ዘመኑ ከርዕደ መሬት አደጋ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሕይወጥ የጠፋበት ክስተት በሚል ተመዝግቧል።