መጋቢት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፉት ሶስት አመታት በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ ይኖሩ በነበሩ በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ትእዛዝ ያስተላለፉት ከፍተኛ ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ባልቀረበቡበት
ሁኔታ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ያሉ ሹማምንት ባለስልጣናት ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጓል።
አቃቢ ህግ ከ55 በላይ የአማራ ተወላጆች እና በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ግድያ እንዲፈጸም አድርገዋል ባላቸው የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪ በነበሩት አቶ ምፍሳፎ ጉይ ፣ የድርጅት ሃላፊው አቶ ተካልኝ ሽፈራው፣ የወረዳው የካቢኔ አባልና የአስተዳዳሪው አማካሪ
አቶ ክፍሌ ሽፈራው እና በሌሎችም 18 የወረዳው ሹማምንትና ነዋሪዎች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19 ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶባቸዋል።
አቃቢ ህግ በአቀረበው የክስ ቻርጅ፣ ተከሳሾች ለበርካታ አመታት በአካባቢው ሰፍረው ይኖሩ እንደነበር ጠቅሷል። ይሁን እንጅ ተከሳሾች ” ይህ ክልል የእኛ በመሆኑ አማሮች በሙሉ ለቃችሁ ውጡ፣ የማትወጡ ከሆነ ግን ያለንን ሃይል ሁሉ ተጠቅመን እናስወጣችሁዋለን
” በማለት ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ” አቃቢ ህግ ገልጿል።
የወረዳው አስተዳዳሪና ባለስልጣኖች አማሮች እስከ 2007 ክልሉን ለቀው የማይወጡ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው መዛታቸውንና ይህንንም ተከትሎ ባለፉት 3 አመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው አማሮች መፈናቀላቸውን፣ መገደላቸውንና ሃብትና ንብረታቸውን
መዘረፋቸውን በክሱ ተመልክቷል።
በአቃቢ ህግ የክስ ቻርች ላይ 55 አማሮች እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የፌደራል ፖሊሶች መገደላቸው እንዲሁም 7 ሰዎች ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማቸው ግምታቸው 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የነዋሪዎች ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ግምታቸው 10
ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የቀንድና የጋማ ከብቶች መዘረፋቸውን ፣ 19 ሺ ኩንታል የሚሆን ምርት መውደሙን ፣ 1 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የእርሻ መሳሪያዎች፣ ከ1 ሺ ሄክታር በላይ ሰብል መውደሙንና ሌሎችም በርካታ ጥፋቶች ተዘርዝረው ቀርበዋል።
በጉራ ፈርዳ የደረሰውን ከፍተኛ መፈናቀል በመቃወም መኢአድ እና ሰመጉ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ቢያወጡም መልስ ሳያገኙ ቆይተዋል። የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ግርማ ሰይፉ በጉራፈርዳ የደረሰው መፈናቀል ” አንድ አገር አለን ብለን እንድናስብ
ያደርገናል ወይ ሲሉ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጠይቀዋቸው ነበር
አቶ መለስ ዜናዊ አማሮች ተፈናቀሉ እያሉ የሚናገሩት በኢትዮጵያ አንድነት እንታወቅ የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መሆናቸውን በመግለጽ፣ በአማሮች ላይ ተፈጸመ የሚለውን ክስ አጣጥለውት ነበር ። ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራ ክልል እና በደቡብ ክልል መካከል
ስምምነት ከተደረሰ በሁዋላ ነው ያሉት አቶ መለስ ይሄ በአማራ ወይም በምስራቅ ጎጃም ነዋሪዎች ላይ የተቃጣ ወንጀል አይደለም ሲሉ የተፈጸመውን ድርጊት ተከላክለው ነበር
ይሁን እንጅ አቶ መለስ ከሞቱ ከ2 አመታት በሁዋላ አቃቢ ህግ ” አማሮች ሆን ተብሎ መገደላቸውን፣ ጥቃቱንም የፈጸሙት የወረዳው ባለስልጣናት መሆናቸውን ዘርዝሮ አቅርቧል።
ምንም እንኳ አቃቢ ህግ የወረዳውን ባለስልጣናት ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረቡ የሚመሰገን ቢሆንም፣ ትእዛዙን የሰጡት የፌደራል፣ የክልልና የዞን ባለስልጣናት ፣ ጥፋቱን ሁሉ በታችኞች ባለስልጣናት ላይ አድርገው ራሳቸውን ከተጠያቂነት ማውጣታቸው ተገቢ
አለመሆኑን አቶ ተስፋሁን አለምነህ የመኢአድ አመራር ተናግረዋል።
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የክልሉ ፕ/ት በነበሩበት ወቅት ያወጡት ህግ ለግጭቱ መንስኤ መሆኑ በወቅቱ ተዘግቧል። አቶ ሽፈራው ማንኛውንም ትእዛዝ የተቀበሉት ከአቶ መለስ መሆኑን ለቀረበባቸው ወቀሳ መልስ ሰጥተው ነበር። አቶ መለስ በህይወት ባይኖሩም አቶ ሽፈራው
ሽጉጤና ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት በክሱ አለመካተታቸው የክሱን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል።
“የዘር ማጥፋትን ክልከላና ቅጣት” በሚለው አለማቀፍ ደንጋጌ ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል የአንድን ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ዘር አባላትን ወይም የሃይማኖት ተከታዮች ሆን ብሎ በከፊል ወይም በሙሉ ማጥፋትን ወይም የማጥፋት ሙከራ ማድረግ፣ የአንድን ቡድን አባላት
መግደል፣ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ በህይወታቸው ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ጥፋት በከፊል ወይም በሙሉ መፈጸም የሚሉትን ወንጀሎች መቀመጣቸውን በመጥቀስ፣ በጉራፈርዳ የተፈጸመው ወንጀልም የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ
የህግ ባለሙያ ገልጸዋል።
ከጉራፈርዳ የተፈናቀሉ ሰዎች የት አካባቢ እንደሰፈሩና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በግልጽ አይታወቅም። የተወሰኑት ወደ መተማ አካባቢ ሄደው እንዲሰፍሩ ቢደረግም በውሃና በመሰረተልማት አቅርቦት ማነስ የተነሳ አብዛኞቹ አካባቢውን ለቀው ሂደዋል።