ባለፉት 4 አመታት ለአባይ ግድብ የታሰበውን ያክል ገንዘብ መሰብሰብ ሳይቻል ቀረ

መጋቢት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ኃይሎች ያሳተፈ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ባለመቻሉ ለአባይ ግድብ ፕሮጀክት ሕዝቡ በቂ ድጋፍ እንዳያደርግ ተጽኖ አድርጎበታል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 4ኛ ዓመት በዓል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግድቡ ባለበት ጉባ ከተማ በመከበር ላይ ሲሆን ባለፉት 4 ዓመታት  ሕዝብን በማንቀሳቀስ ለግድቡ ግንባታ የተሰባሰበው መዋጮ ወይንም የቦንድ ሽያጭ 6 ቢሊየን ብር ያህልብቻ

መሆኑ የመንግስትን ኪሳራ የሚሳይ መሆኑን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሮ ባጠናከረው ዘገባ አመልከቷል፡፡

ከ4 ኣመታት በፊት ለጠቅላላ ግንባታው 80 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ እንደሚስፈልግ የተገመተ ሲሆን ፣ ወጪውን  በሕዝብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ መሸፈን  ያልተቻለው፡ መንግስት ሁሉን ያሳተፈ ብሔራዊ መግባባት ማምጣት ባለመቻሉና የግድቡን ስራ ለፖለቲካ ዓላማ

እያዋለው በመምጣቱ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡

በግድቡ ግንባታ ጉዳይ መንግስት ራሱን ከፍ አድርጎ ተቀናቃኞቹን በማጣጣል የሚከተለው ስትራቴጂ የልዩነት አድማሱን እንዳሰፋው የጠቆሙት አንድ ምሁር፣  በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች ግልጽ ድጋፍ በመስጠት ሕዝቡ የግድቡን ግንባታ እንዲደግፍ

የበኩላቸውን እገዛ ከማድረግ መታቀባቸው፦ ሕዝብ የተስተካከለ ዕይታ እንዳይኖረው አድርጎአል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡ በየኢኮኖሚ አቅማቸው የተሻሉ ናቸው ተብለው የሚገመቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና

ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከግድቡ በፊት ዳቦ እና የሰብኣዊ መብት ጥበቃ እንዲሁም የዴሞክራሲና የህግ የበላይነት አጀንዳዎችን ደጋግመው በማንሳታቸው በገዥው ቡድን እንደአክራሪ ኃይል መፈረጃቸው፦ ተሳትፎአቸው እንዲገደብ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉንም

ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ምክንያት በተለያዩ በአሜሪካና በአውሮፓ ሀገራት በከፍተኛ ባለሰልጣናት  የታገዙ ቦንድ ማሰባሰቢያ መድረኮች የፖለቲካ ውዝግቦችን በማስተናገድ መክሸፋቸውን በማስታወስ ይህ ተደጋጋሚ ክስተት መንግስት ቆም ብሎ አካሄዱን እንዲመረምር ከማስገደድ

ይልቅ ደንግጦ ብቻውን እንዲቆም ማድረጉ ሌላው ችግር ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

ኢህአዴግ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ የታቀደውን የአባይ ግድብ እቅድ የራሱ በማድረግ ዕውቅና ከመንፈግ ጀምሮ በሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማሳተፍ እንኩዋን ፍላጎት ማጣቱንም አመልክተዋል፣

የተቃውሞ ኃይሎች አፍራሽ ሚና ብቻ እንዳላቸው አድርጎ መሳሉ ሁሉም ወገኖች በልማት ጉዳይ ላይ እንኩዋን እንዳይስማሙ እንቅፋት መፍጠሩንም አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በወጣትነት ለስራ የደረሰ ዕድሜ ላይ እንደሚገኝ ያስታወሱት ምሁሩ መንግስት ራሱ ተዋጥቶልኛል ያለውን 6 ቢለየን ብር አምነን ከሕዝብ ቁጥር ጋር ስናሰላው የተገኘው ውጤት እጅግ ደካማ መሆኑን ያሳየናል ብለዋል።

መንግስት የአባይ ግድብን ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ በሩን ቢከፍትና ቢያሳትፍ እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባትን ቢፈጥር የተሻለ ስራ መስራት ይቻላል ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

ከውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን 1 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ እቅድ የተያዘ ቢሆንም፣ እስካሁን የተሰበሰበው በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

አንዳንድ ወገኖች  መንግስት በቅርቡ ከግብጽ ጋር ያደረገውን ስምምነት ተከትሎ ግድቡን ለመጨረስ፦ ምናልባትም ከአንዳንድ አበዳሪ ድርጅቶች ገንዘብ ሊበደር ይችላል በማለት አስተያየት ይሰጣሉ።