የምዕራብ አየር ምድብ የሁሉንም ቋንቋ ተናጋሪዎች በእኩልነት ያላማከለ የማዕረግ እድገት መስጠቱ በአየር ምድቡ ውስጥ ቅሬታ ፈጠረ

መጋቢት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስራ አፈፃፀማቸው ብልጫ አመጥተዋል እንዲሁም የመቆያ ጊዜያቸውን ሸፍነዋል ለተባሉ  የአንድ አካባቢ ተወላጅ ከፍተኛ መኮንኖች፣መሰረታዊ መኮንኖችና ለባለ ሌላ ማዕረግተኞች  የማእረግ እድገት ተሰጥቷል።

መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በምድቡ ወታደራዊ መዝናኛ ክበብ በተዘጋጀው የማዕረግ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት የምድቡ ታማኝ ሰዎች ብቻ የተገኙ ሲሆን ፣ ስነስርዓቱ ለሁሉም የሚዲያ ሰዎች ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።

ለተሸላሚዎቹ ማዕረግ የሰጡት የምድቡ አዛዡ ኮሎኔል ይልማ መርዳሳ በእለቱ ለተሰባሰቡት የስርዓቱ ደጋፊዎች  እንደተናገሩት የማዕረግ እድገት የስራ ታታሪነትንና ታማኝነትን እንዲሁም ኃላፊነትን ስለሚጨምር በዕለቱ ማዕረግ ያገኛችሁም ሆነ ወደፊትም የምታገኙ ምድብ

የሰራዊት አባላት አሁን የጀመርነውን ውጤታማ ስራ አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁ በማለት በእለቱ ማእረግ ያላገኙ  የአየር ኃይል አባላትን የሚያጽናና  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የእለቱ ማዕረግ አሰጣጥ ፍትሃዊ አልነበረም በማለት ለዘጋቢያችን መረጃውን ያስተላለፉት አባላቱ፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉት ሽልማቶች ወደ አንድ አካባቢ ያነጣጠሩ መሆናቸው አባላቱን ያስከፋ ድርጊት ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአየር ሃይል አባላት መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ለመቆጣጠር ያልቻለው መንግስት፣  በፖለቲካ አመለካከት የተነሳ እየተከፋፈሉ የመጡትን አባላት  ወደ አንድነት ለማምጣት እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ሲጠበቅ ልዩነቱን የሚያሳፋ ድርጊት በመፈጸም

ላይ መሆኑን አባላቱ ይገልጻሉ።

የአየር ሃይል አዛዦች ክፍፍሉን የሚጠቀሙበት ታማኝ የሆኑትንና አልሆኑትን ለመለየት ሳይሆን እንደማይቀር አባላቱ አክለው ይገልጻሉ።

የምእራብ እዝ የማእረግ አሰጣጡን ከሚዲያ በማራቅ በዝግ ለማድረግ የተገደደው ትችቶችን በመፍራት መሆኑን ምንጮች አክለው ተናግረዋል።