ታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-ፓርቲውን ከመሠረቱት ግለሰቦች መካከል መርህ ይክበር በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት ይገኙበታል፡፡
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ቃል አቀባይ አቶ አርዓያ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እሑድ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት በተካሄደው መሥራች ጉባዔ 150 ሰዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር አባል አቶ ይልቃል ጌታሁን የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ሰላሳ ሰባት አባላት ያሉት የፓርቲው ምክር ቤትም ተቋቁሟል፡፡
በፓርቲው መሥራች ጉባዔ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳና ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ተገኝተዋል፡፡
አቶ አርዓያ እንዳሉት፣ አዲስ የተመረጠው አካል አሥራ ሁለት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካቋቋመ በኋላ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ለምርጫ ቦርድ የሕጋዊነት ጥያቄ ያቀርባል፡፡
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በቀለም የተሰየመ ፓርቲ ተመሥርቶ ስለማያውቅ፣ ሰማያዊ የሚለውን ስያሜ ለምን መረጣችሁ? በሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ አርዓያ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድነት፣ ነፃነት፣ ፍትሕ የሚሉ ነገሮች ይበዙበታል፡፡ እኛ ግን በስም ሳይሆን በተግባር ማሳየት እንፈልጋለን፤›› በማለት ለየት ያለ ስም መምረጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰማያዊ ቀለም አንድነትን፣ ሰላምንና ተስፋን እንደሚገልጽ የጠቆሙት አቶ አርዓያ፣ ‹‹እኛ በሰላማዊ ትግል የምናምን ነን፡፡ በፓርቲው ውስጥ ወጣቶች በብዛት ተሳትፈዋል፡፡ ለነገ ወጣቶች ተስፋ እንሆናለን ብለን ስለምናምን ነው ሰማያዊ ቀለምን የመረጥነው፤›› በማለት ሰማያዊ የሚለው ስያሜ የአባላቱን መንፈስና ስሜት የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መርህ ይከበር በሚል ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት መካከል አንዱ አርቲስት ደበበ እሸቱ ነበር፡፡ በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ ከታሰረ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የተፈታው አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተላለፈው ‹‹አኬልዳማ›› በተሰኘው ፕሮፓጋንዳ ላይ መታየቱን አስመልክቶ የተጠየቁት
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ቃል አቀባይ አቶ አርዓያ ፣ አርቲስት ደበበ በፓርቲው መሥራች ጉባዔ ላይ እንዲገኝ የተጋበዘው ፤በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ሰው በመሆኑ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹አርቲስት ደበበ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በጣም ትልቅ ተሳትፎ አለው፡፡ በሕይወት ካሉት አርቲስቶች ትልቅ የሚባለው እሱ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ የምናየው ትላልቅ ሰዎችን ማዋረድና ክብራቸው ዝቅ እንዲል ማድረግ ነው፡፡ አገሪቷ ላይ ትልቅ ሰው እንዳይኖር የማድረግ ዓላማ ይመስለኛል፤›› ማለታቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ በረከት ስምኦን “አኬልዳማ” የተሰኘውን ድራማ የሰራነው፣ የአለማቀፍ ማህበረሰቡና የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች መንግስት ግለሰቦችን ያሰረው ስልጣኑን ለማቆየት ሲል ነው በማለት እየሰጡት ያለውን አስተያየት ለመከላከል ነው”ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሀንና ፖለቲከኞች እስረኞችን በተመለከተ እየሰጡት ያለው አቋም፣ እነርሱኑ መልሶ የሚጎዳቸው መሆኑን አቶ በረከት ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ አኬልዳማ የእሰረኞችን መብት የሚገፍ መሆኑን እያወቁ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ በአጠቃላይ ችግር አለበት በማለት አልፈውታል።