ሶማሊ-ላንድ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የተመዘገቡ 20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስገድዳ ወደ ኢትዮጵያ መለሰች

ታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-ሶማሊ-ላንድ  በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የተመዘገቡ 20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን  አስገድዳ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጓን ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለጠ። ዳግም የዚህ ዓይነት ድርጊት እንዳትፈጽምም ጠይቋል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር  ባለፈው ዲሴምበር 28፤  የሶማሊላንድ አስተዳደር  ለመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ወደ ሶስተኛ አገር የጥገኝነት ጥያቄ እንዲሰጣቸው አመልክተው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉትን 20 ኢትዮጵያውያን በሀይል በማስገደድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

ይህ ድርጊት  “ስደተኞችን ወደማይፈልጉት፤ለነፃነታቸውና ለህይወታቸው አስጊ ወደሆነ ስፍራ አስደድዶ መመለስ የተከለከለ ነው” የሚለውን  ዓለማቀፉን የስደተኞች  መብትና ህግጋት የጣሰ መሆኑንም ሂዩማን ራይትስ ዎች አመልክቷል።

የሶማሊ ላንድ የአገር ውስጥ ሚኒስትር በበኩሉ ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጧል።

ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ተገድደው ከመመለሳቸው በፊት  “ዋጃሌ” ተብሎ በሚጠራው በኢትዮጵያ የቦርደር ከተማ በሚገኘው የስደተኞች ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከዓለማቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ጋር መገናኘታቸውም ተገልጿል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል በቀለ፦”ሱማሌ ላንድ የስደተኞችን መሰረታዊ መብቶች ልትጠብቅና ልትንከባከብ እንጂ፤ልትገስስ አይገባም”ብለዋል።

አቶ ዳንኤል አክለውም፦” ስደተኞቹን በማስገደድ እንዲመለሱ ያደረገው አካል በቶሎ መጠየቅ አለበት። የአገሪቱ አስተዳደርም የዚህ ዓይነት ድርጊት እንደማይፈጸምም ሊያረጋግጥና ዋስትና ሊሰጥ ይገባል”ብለዋል።

ሶማሌ ላንድ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙት ከ 28 ሺህ በላይ ስደተኞች መካከል፤አብዛኞቹ  ኢትዮጵያውያን ናቸው።