(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 9/2010)
በወልቂጤ ለሶስተኛ ቀን በቀጠለው ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ተገደሉ።
በወልቂጤ የተጀመረው አድማና ተቃውሞ ወደ ሌሎች የጉራጌ ዞን ወረዳዎች መዛመቱ ታወቋል።
ጉብሬና አገና በተባሉ አካባቢዎች ዛሬ ሙሉ በሙሉ የስራ ማቆም አድማ ተደጓል።
የአገና ወራዳ ከተማ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ነው ተብሏል።
በእንድብር የልዩ ሃይል ሰራዊት ከተማዋን በመቆጣጠር የህዝቡን ተቃወሞ ለማፈን እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታወቋል።
በወልቂጤ የጀመረው የጉራጌ አብዮት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ደርሷል።
በኧዣ ወረዳ አገና ከተማን ጨምሮ በ27ቱም ቀበሌዎች ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ እያደረገ መዋሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በጉብሬ ወረዳም ህዝባዊ እምቢተኝነት መቀስቀሱን ከአካባቢው ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሁለቱም ወረዳዎች የስራ ማቆም አድማው በተጠናከረ ሁኔታ የተጀመረ ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ተገተው መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በጉብሬ የአድማውን ጥሪ ባለመቀበል ሲንቀሳቀስ የነበረ የባጃጅ ታክሲ ላይ ርምጃ ተወስዶ እንዲቃጠል መደረጉም ታውቋል።
በአገና የስርዓት ልውጥ እንፈልጋለን በማለት አደባባይ የወጣው ህዝብ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር በስልጣን ላይ ያለው መንግስት አርጅቷል፣ በአስቸኳይ ይውረድ የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰማ እንደነበር የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ህዝቡ ትግል ተጀምሯል አዋጅ አያግደንም በማለት አቋሙን የሚያሳዩ መልዕክቶችን አሰምቷል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንነሳ ሲሉም ጥሪ አድርገዋል።በአገና ከተማ ሁሉ ነገር ተዘግቷል::
ሶስት ወጣቶች ትላንት ታስረው የነበረ ቢሆንም ዛሬ ጠዋት ህዝቡ በሃይል እንዲፈቱ ማድረጉን ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የስልክ ኔትወርክና ኢንተኔት መዘጋቱ እንቅፋት ፈጥሯል ያሉት የአድማው አስተባባሪዎች ህዝቡ በባህላዊ መንገድ ተጠቅሞ የአድማ ጥሪውን እየተቀባበለው በመሆኑ በሁሉም የጉራጌ ወረዳዎች አድማና ተቃውሞው ሊዛመት እንደሚችል ነው የሚገልጹት።
በእምድብር ተመሳሳይ የህዝብ ንቅናቄ ሊጀመር እንደሚችል የተገነዘበው አገዛዙ ትላንት ማምሻውን የፌደራል ፖሊስ ሃይሉን ወደ ከተማዋ ማስገባቱን ለማወቅ ተችሏል።
ወልቂጤ በአድማና ተቃውሞ ሶስተኛ ቀኗን ይዛለች።
ወደ አደባባይ ተቃውሞ ከተቀየረበት ከትላንት ጀምሮ በትንሹ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ ሁለት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በአድማው ያልተሳተፈ አንድ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት መድረሱም ተገልጿል።
የጉራጌውን አብዮት በተመለከተ ከአገዛዙ የተሰጠው መግለጫ በመልካም አስተዳደር እጦትና በዘገየ የልማት ጥያቄ የተከሰተ የህዝብ ተቃውሞ መሆኑንም አስታውቋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የጉራጌ ዞን የተለያዩ ነዋሪዎች ግን ዋናው ጥያቄ የስርዓት ለውጥ መሆኑን ይገልጻሉ።
የህወሃት አገዛዝ ከስልጣን እስኪወርድ ትግሉ ይቀጥላል ብለዋል ነዋሪዎቹ።