በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የታሰሩ ተማሪዎች ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ሂውማን ራይትስ ሊግ አስታወቀ

ግንቦት ፲፰(አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ከእስር ቤቶች የሚወጡት መረጃዎች አስደንጋጭና አሳሳቢ ናቸው ብሎአል።

እስረኞቹ እጆቻቸውን ወደ ሁዋላ  ታስረው  ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገኛኑ በማድረግ   የተለያዩ ማሰቃያዎች እየተፈጸሙባቸው እንደሆነ የሚገልጸው የሰብአዊ መብት ሊግ፣ አስከፊ የተባለ ስቃይ ከደረሰባቸው 10 ተማሪዎች መካከል ተማሪ ተስፋየ ቱፋ እና ባናቱ ሃይሉ ይገኙበታል።

በምእራብ ወለጋ የተያዙ 50 እስረኞች የደረሱበት አለመታወቁን ከእነዚህም መካከል 15 ቱ ሴቶች መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

ከዚሁ አካባቢ የተያዙና ወደ ማእከላዊ እስር ቤት ሊወሰዱ ይችላሉ የተባሉ የ9 ሰዎችን ስም ዝርዝርም ይፋ አድርጓል።

በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ይዞ ማሰርና ማሰቃየት መቀጠሉን በቅርቡ ከታሰሩት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑትን ዘርዝሮ አቅርቧል።

ድርጀቱ ተማሪዎቹ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ ተማሪዎችን ማሰር፣ መግደልና ማሰቃየት እንዲቆም፣ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋምና ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።