መድረክ በአዲስ አበባ ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄደ

ግንቦት ፲፰(አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተለያዩ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክ በኢትዮጵያ ውስጥ “ለሰላማዊ ተቃውሞ የጥይት መልስ አይሰጥ” በሚል አላማ ያካሄደው ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ሰልፈኞቹ “ነጻነት እንፈልጋለን” ፣ “ቢሉስማ ኒበርባና “፣ ዲሞክራሲ እንሻለን፣ ገለልተኛ የምርጫ ስርአት ይኑር፣ የታሰሩት የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች ይፈቱ፣ አትግደሉን፣ አትዋሹን፣ ለመብት መታገል ሽብርተኝነት አይደለም፣ የዜጎች በግፍ መፈናቀል ይቁም የሚሉ መፈክሮች በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ አሰምተዋል።

እጅግ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሌሎች የፖለቲካ ድርጀቶች መሪዎችም ተገኝተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ 12 የመድረክ አባሎች በቡራዩ ታስረው እንደሚገኙና ይህን ዜና እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ አለመፈታታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት  የመድረክ ስራ አስፈጻሚ እና የህዝብ ግንኙነት ክፍል አባል የሆኑትን አቶ ጥላሁን እንዳሻውን በሰልፉና በቡራዩ ስለታሰሩት ሰዎች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።