(ኢሳት ዜና–ሕዳር 18/2010)በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንደገና ባገረሸው ግጭት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተሳታፊ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ንጹሃን ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድሉ በነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይም ርምጃ መወሰዱ ታውቋል።
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ እንደገና ግጭት ማገርሸቱን መንግስት በሳምንቱ መጨረሻ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዲስ ባገረሸው ግጭት ባለፈው ሳምንት ብቻ 20 ሰዎች መገደላቸውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ሲገልጹ የኢሳት ምንጮች በግጭቱ የሞቱት ቁጥር ወደ 70 ማሻቀቡን አመልክተዋል።
በተለይ በሞያሌ ወረዳ በነበረው ግጭት 2 የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑ ኮማንዶዎች መገደል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የአጸፋ ጥቃት ማስከተሉም ተመልክቷል።
ቅዳሜ ህዳር 16/2010 ቦርቦር በተባለው አካባቢ በነበረው ግጭት ደግሞ የሶማሌ ልዩ ሃይል መለዮን የለበሱ ፖሊሶች በብዛት ሲገደሉ ሶስት የመከላከያ ሰራዊት አባላትም መገደላቸው ታውቋል።
በሰሞኑ ግጭት በአጠቃላይ 5 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገደሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ዕልቂት ወደ 70 ማሻቀቡን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በመከላከያ ሰራዊቱ አባላትና በሶማሌ ልዩ ሃይል ላይ እያደፈጠ ጥቃት የሚሰነዝረው ሃይል ማን እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም።
ይህ ቡድን የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለሚያደርሱት ጥቃት አጸፋ በመስጠት ላይ መሆኑም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሳምንቱ መጨረሻ አሬሮ አካባቢ በአንድ ስፍራ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በድንገት በተከፈተ ተኩስ ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 7 ሰዎች መገደላቸውን የኢሳት ምንጮች ከስፍራው ገልጸዋል።
አምና ሚያዚያ ላይ የተባባሰው የኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ግጭት እንደገና መስከረም ላይ ማገርሸቱ ይታወሳል።
መፍትሄ አገኘ ከተባለ በኋላ እንደገና በሳምንቱ መጨረሻ የተቀሰቀሰበት ምክንያት አልታወቀም።
በቀደመው ግጭት ተሳታፊ የሆኑ 98 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል ሲታሰሩ 5 ሰዎች ደግሞ ከሶማሌ ክልል መታሰራቸውን የመንግስት ቃል አቀባይ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በሳምንቱ መጨረሻ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።