በታላቁ ሩጫ ኮከብ የሌለበት ባንዲራ በፖሊስ ሲቀማ ዋለ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 18/2010)በታላቁ ሩጫ ውድድር ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ የያዙ ኢትዮጵያውያን በፖሊስ ሲነጠቁ መዋላቸውን በስፍራው የነበሩ ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

የቴዲ አፍሮን ምስልና “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን የዜማውን አርማ የያዘ ካኒቴራ የለበሱ ወጣቶችም ከታላቁ ሩጫ ውድድር እንዲወጡ ተደርገዋል።

የሼህ መሀመድ አላሙዲ አድናቂዎች “አይዞህ አባቴ”የሚልና የእሳቸውን ፎቶ ለጥፈው ሲሮጡ ግን ከውድድሩ እንዲታገዱ አልተደረጉም።

በታላቁ ሩጫ ላይ 44ሺህ ተሳታፊዎች ለውድድሩ ድምቀት ሰጥተውት ነበር።

በዚህ ውድድር ላይም ብዙዎቹ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መገለጫ የሆነውን የአረንጓዴ፣ቢጫ ቀይ ቀለማት በተለያዩ ሁኔታዎች አንጸባርቀዋል።

ቀለማቱን እጃቸው፣ግንባራቸው፣ጸጉራቸውና በአለባሳቶቻቸው ላይ ያንጸባረቁት የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች በፖሊስ ሲንገላቱ ታይተዋል።

ችግሩ ደግሞ የሕወሃት መንግስት ፖሊሶች ለምን ኮከብ ያለበትን ባንዲራ አልያዛችሁም ቀለማቱም ይህንን አላካተቱም በሚል እንደሆነ ነው የተነገረው።

ይህ የፖሊስ ርምጃ ብዙዎችን አበሳጭቷል።

አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማችን አባቶቻችን ጠላትን ተዋግተው ድል ያደረጉበት አርማና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው ቢሉም ሰሚ አላገኙም።

የፌደራል ፖሊስ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ ከሯጮቹ ላይ በሃይል በመቀማት አንድ ላይ ሲጥሉት ለማየት ተችሏል።

ፊታቸው፣እጃቸውና ጸጉራቸው ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተቀቡትን ግን ፖሊሶች ምንም ለማድረግ አልቻሉም።

ይህ በዚህ እንዳለም የታዋቂው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮን ምስል የለበሱና ኢትዮጵያ የተሰኘውን አልበም አርማ ያነገቡ ወጣቶች ከታላቁ ሩጫ ውድድር መባረራቸው ነው የተነገረው።

ወጣቶቹ ከውድድሩ ቢባረሩም ተሳታፊዎቹ ለቴዲ አፍሮና ለኢዮጵያዊነት አልበሙ ያላቸውን አድናቆት ሲያስተጋቡ ታይተዋል።

የተባረሩትን ወጣቶች ሌሎቹ የውድድሩ ተሳታፊዎች በአድናቆትና በጭብጨባ ሲያጅቧቸው የታየበት ሁኔታም ነበር።

በተቃራኒው ግን የሼህ መሀመድ አላሙዲን መታሰር ያንገበገባቸው የአገዛዙ ደጋፊዎች የእሳቸውን ምስል ጀርባቸው ላይ ለጥፈው አይዞህ አባቴ ሲሉ በፖሊስ አልተነኩም።

በሁኔታው ግራ የተጋቡ ተሳታፊዎችም የፖሊስን አድሏዊነትና ሚዛናዊ አለመሆን በመታዘብ ፖሊስ የማን ነው ሲሉ አርፍደዋል።

የታላቁ ሩጫ በሰላም መጠናቀቁ ሲገለጽ ሁለት ተሳታፊዎች ብቻ ከጤና እክል ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።