ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከህወሃት ስራ አስፈጻሚ አባልነት ታገዱ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 18/2010)ከሁለት ወራት በላይ የዘለቀው የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤትን ወይዘሮ አዜብ መስፍንን አገደ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው የፓርቲውን ሊቀመንበርና ሌላ አንድ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዝቅ ማድረጉን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን አስታውቋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሊቀመንበርነትን ላለፉት አምስት አመታት የያዙት አቶ አባይ ወልዱ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ እንዲሉ በመደረጋቸው ሊቀመንበርነቱንም ለሌላ ግለሰብ ማስረከብ ግዴታቸው ይሆናል።

በዚህ መሰረት ሕወሃት በቀጣዮቹ ቀናት ሌላ የፓርቲ ሊቀመንበር እንደሚመርጥ ይጠበቃል።

የአሁኑ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የመሪነቱን ስፍራ ሊይዙ ይችላሉ ሲሉ አንዳንዶች ግምታቸውን ሰጥተዋል።

በብዙዎቹ የህወሃት አባላት ዘንድ በፖለቲካ ንቃታቸውና በሕዝብ የማሳመን ችሎታቸው ጥያቄ ስለሚነሳባቸው ከርሳቸው ይልቅ ሌላ ግለሰብ እንደሚመረጥ ይጠበቃል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ሕወሃት/ማዕከላዊ ኮሚቴ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ከፓርቲው ስራ አስፈጻሚነት እንዲሁም ከማዕከላዊ ኮሚቴ ማገዱን ተከትሎ ከኢፈርት ዋና ስራ አስፈጻሚነት እንደሚያነሳቸውም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሀብት የተከማቸበት በሚል የሚጠቀሰው ኢፈርት በቢሊየን ብሮች የሚንቀሳቀስ ሲሆን በዚህ ላይ የሚደረጉ ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚኖሩ ምንጮች ይገልጻሉ።

ወይዘሮ አዜብ መስፍን ሌሎች ተጨማሪ ርምጃዎችም ሊገጥማቸው እንደሚችል ተመልክቷል።

አቶ አባይ ወልዱም ከሕወሃት ሊቀመንበርነቱ ባሻገር የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትነቱንም ሊያጡ እንደሚችል በመገለጽ ላይ ነው።

አንዳንድ ምንጮች ዶክተር አርከበ እቁባይ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ በመግለጽ ላይ ናቸው።

ሆኖም አቶ አርከበ እቁባይ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው በሕጋዊ አጋባብ ከሄዱ መንገዱ ዝግ እንደሚሆንም መረዳት ተችሏል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው አንድ ገጽ መግለጫ ከአቶ አባይ ወልዱና ከወይዘሮ አዜብ መስፍን በተጨማሪ አቶ በየነ ምክሩ የተባሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከስራ አስፈጻሚነታቸው ተወግደዋል።

ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ ሁለት አባላት ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።

የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዘጠኝ ሲሆኑ ሶስቱ ዝቅ ብለውና ታግደው ሁለቱ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ጥያቄ ያልተነሳባቸው አራት ብቻ ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ አንዱ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው የሄዱት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በመሆናቸው ጥያቄ ያልተነሳባቸው ሶስት ብቻ እንደሆኑም መረዳት ይቻላል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ሂስና ግለሂስ መድረክ መቀጠሉም የተገለጸ ሲሆን ሒደቱ ሳያልቅ መግለጫው የወጣበት ምክንያት ግን ግልጽ አልሆነም።