(ኢሳት ዜና–ሕዳር 6/2010) በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከአለም አቀፍ መመዘኛ በታች መሆናቸውን አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ገለጹ።
የቻይናው ዜና አገልግሎት ዥንዋ በኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የፕላኒንግ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ኤልያስ ግርማን ጠቅሶ እንደዘገበው 89 በመቶ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ከአለም አቀፍ መመዘኛ ዝቅ ያሉ ሆነው ተገኝተዋል።
በሰው ሃይል፣በትምህርት አሰጣጥ፣በመሰረተ ልማት፣በተማሪዎቹ ብቃት በአጠቃላይ በሀገሪቱ በተደረገ ጥናት 30 ሺ 605 ትምህርት ቤቶች ከአለም አቀፍ መመዘኛ በታች ሆነው ናቸው።
ይህም በሀገሪቱ ካሉ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች 89 በመቶውን እንደሚሸፍንም ይፋ አድርገዋል።
የፕላኒንግ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ወሳኝ የሆኑ መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ በተደረገ ጥናት አለም አቀፍ መስፈርትን አሟልተው አገልግሎት የሚሰጡት የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች 11 በመቶ ብቻ ናቸው።