የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በከፍተኛ ውዝግብና ቀውስ መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 6/2010) ከአንድ ወር በላይ የዘለቀው የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በከፍተኛ ውዝግብና ቀውስ ውስጥ መቀጠሉን የሕወሃት ደጋፊዎች ይፋ አደረጉ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውም ታውቋል።

ውዝግቡ በሰላም እንዲቋጭ የሕወሃት ደጋፊዎች ተማጽኖ በማቅረብ ላይ ናቸው።

ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በመቀሌ እንዲሁም በሶስተኛውና በአራተኛው ሳምንት በአዲስ አበባ ያደረጉት ስብሰባ ሊቋጭ አልቻለም የወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪዎች።

የመሪዎቹ ስብሰባ ወደ ስምምነት ሊያመራ ባለመቻሉም ከ10 ቀናት በፊት እንደገና በመቀሌ የተቀመጡት የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪዎች አሁንም በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ መገኘታቸውን የጻፉት ሁለት የሕወሃት ደጋፊ ድረገጾች ናቸው።

ጥቅምት 10/2010 መቀሌ በተጀመረው የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ባለሃምሳ ዘጠኝ ገጽ የግምገማ ሪፖርት ለውይይት መቅረቡን “ሆርን አፌርስ” የተባለው የሕወሃት ደጋፊ ድረገጽ ገልጿል።

ይህንን ሰነድ በስብሰባው ከተገኙት ከ8ቱ የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት 5ቱ ሲቀበሉት ሶስቱ እንደተቃወሙት ምንጮቹን ጠቅሶ ጽፏል።

ከተቃወሙት ውስጥ አንዷ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን መሆናቸው ታውቋል።–ከተቃወሙት ሁለቱ ግን እነማን እንደሆኑ ይፋ አልሆነም።

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሰነዱን 5 ለ3 በሆነ ድምጽ የተቀበለው ውጥረት ከተመላበት ስብሰባ በኋላ እንደሆነም ተመልክቷል።

ይህው ሰነድ በማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ለውይይት ሲቀርብ ሁሉም በስምምነት እንዳሳለፉት ሆርን አፌርስ ዘግቧል።

በስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ላይ ሰነዱን የተቃወሙት ሶስት ሰዎች ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ እንዴት ስምምነታቸውን እንደገለጹ በዘገባው አልተብራራም።

ፓርቲውን፣መንግስታዊ አስተዳደሩን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን የሚፈትሸውን ባለ 59 ገጽ ሰነድ ከመነሻው የተቃወሙት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ትላንት በቀጠለው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ ረግጠው መውጣታቸውን የጻፈው ሆርን አፌርስ የተባለው አፍቃሬ ሕወሃት ድረ ገጽ ነው።

ወይዘሮ አዜብ መስፍን ስብሰባውን ረግጠው የወጡት ሂስና ግለሂስ በሚካሄድበት ወቅት እንደሆነም ታውቋል።

አይጋ ፎረም የተባለው የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ድረገጽ ባለፈው ሳምንት ወደ ስምምነት ማምራታቸውን ዘግቦ ነበር።

ዛሬ ባወጣውና ባሰራጨው ዘገባ ግን ከስብሰባው በጎ ነገር አለመሰማቱንና ይልቁንም አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን እየቀሰረ በተካረረ ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸውን አመልክቷል።

የሕዝቡን ፍላጎት ከማየት ይልቅ መወነጃጀልን መርጠዋል በማለት የሚወቅሰው አይጋ ፎረም ድረገጽ ብቃት ያላቸውና የተማሩ ወደፊት እንዲወጡና ተሀድሶ ወይንም ሪፎርም እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል።

ከሁሉም በላይ ሕዝቡ የሚፈልገው አንድነታቸውንና ትክክልኛ አቅጣጫ መያዛቸውን ነው በማለት ተስማምተው እንዲወጡ በአደባባይ ተማጽኗል።

የሕወሃት ደጋፊዎች የሕወሃትን ችግር በአደባባይ የሚጽፉት በግልና በቡድን ውስጥ ለውስጥ የሚያደርጉት ግፊትና ተማጽኖ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር መሆኑንም ከቀደሙ ልምዶች መረዳት ይቻላል።

ከ17 አመት በፊት ሕወሃት ለሁለት ሲሰነጠቅ ሪፖርተር ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ የተማጽኖ ዘገባ ማቅረብ የጀመረው እነ አቶ ስዬ አብርሃ የመቀሌውን ስብሰባ ረግጠው ከወጡ በኋላ መሆኑም ይታወሳል።

በእርቅ ስም በተጀመረው ሂደት የበላይነታቸው እየተሸረሸረ የሚገኘው እነ አቶ አባይ ወልዱ ስልጣናቸው እንደማይነካ ዋስትና እንደተሰጣቸው የሚገልጹ ምንጮች አሉ።

ወይዘሮ አዜብም ከኢፈርት ሊቀመንበርነት ለጊዜው እንደማይነሱ ዋስትና ቢሰጣቸውም ሂደቱን ባለማመን ረግጠው መውጣታቸው ተመልክቷል።

በእስካሁኑ ሂደት የእነ አቶ ስብሃት ቡድን የበላይነት የያዘ ቢመስልም የትኛውም ወገን ሙሉ በሙሉ አሸንፎ አለመውጣቱ በመነገር ላይ ነው።

በዚህም ሁለቱም ወገን በሰራዊቱ ውስጥ ደጋፊዎቻቸውን ለማበራከት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ነው የተመለከተው።

እነ አቶ ስብሃት ነጋ፣ከጄኔራል ሳሞራ ጀርባ ደጋፊዎቻቸውን እያደራጁ መሆናቸውም እየተገለጸ ይገኛል።