ሮበርት ሙጋቤ በቤታቸው በቁም እስር ላይ መዋላቸው ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 6/2010)የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በቤታቸው በቁም እስር ላይ መዋላቸው ተሰማ።

የሀገሪቱ ወታደራዊ አዛዦች የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማሰራጫዎችን መቆጣጠራቸው ተሰምቷል።

እንደ አዝጋሚ መፈንቅለ መንግስት እየተቆጠረ ያለውን ይህን ከፊል የሀገሪቱ ነዋሪዎች እንደ መልካም ዜና ወስደውታል ተብሏል።

ዚምባቡዌ ከእንግሊዝ ነጻ ከወጣችበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1980 ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩት የ93 አመቱ ሮበርት ሙጋቤ ከዛሬ ጀምሮ በመኖሪያቸው በቁም እስር ይገኛሉ።

ሙጋቤ የሀገራቸው ወታደራዊ አዛዦች በቁም እስር ላይ እንዳዋሏቸው ለደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ደውለው እንደነገሯቸው ቢቢሲ ዘግቧል።

ሙጋቤ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ለዙማ ነግረዋቸዋል።

ባለፈው ሳምንት ሙጋቤ ምክትላቸውን ኤመርሰን ናንጋግዋን ከስልጣን ማስወገዳቸውን ተከትሎ በዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው ትርምስ ወታደራዊ አዛዦችን ጣልቃ እንዲገቡ አድርጓል።

ሙጋቤ ምክትላቸውን አስወግደው ባለቤታቸው ስልጣኑን እንዲረከቡ እያመቻቹ ባሉበት ሁኔታ ነው ወታደራዊው ክፍል ጣልቃ የገባው።

የሀገሪቱ ወታደራዊ አዛዦች የዚምባቡዌን ሬዲዮና ቴሌቪዥን ማሰራጫዎች መቆጣጠራቸውም ተሰምቷል።

ውሜጀር ጄኔራል ሲቡሲሶ ሞዬ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው እነሱ ኢላማ ያደረጉት በሙጋቤ ዙሪያ በተሰበሰቡትና በሀገሪቱ ለተከሰተው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ተጠያቂ በሆኑት ወንጀለኞች ላይ ብቻ ነው ብለዋል።-ይህንን ተልኳቸውን እንደፈጸሙም ነገሮች እንደሚረጋጉ ተናግረዋል።

ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ወታደራዊ ሃይሉ የሀገሪቱን የገንዘብ ሚኒስትር በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተሰምቷል።

የወታደራዊውን ክፍል ርምጃ ማን እንደሚመራው ለጊዜው ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሆኑትና ባለፈው ሳምንት ቻይናን ጎብኝተው የተመለሱት ጄኔራል ኮንስታኒትኖ ቺዌንጋ ባለፈው ሰኞ እንደገለጹት ወታደራዊው ክፍል በዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የስልጣን ሽሚያና አላግባብ የሆነ ተቀናቃኞችን የማስወገድ ርምጃ እናስቆማለን ብለዋል።

በአንዳንዶች ዘንድ እንደ አዝጋሚ መፈንቅለ መንግስት እየተቆጠረ ያለውን ይህን የወታደራዊ ክፍል ርምጃ ከፊል የሀገሪቱ ነዋሪዎች እንደ መልካም ዜና ቆጥረውታል።

“የተሻለ ሕይወት ይኖረናል መጪው ገናን በጉጉት እንጠብቃለን” ብላለች አንዲት የሐራሬ ነዋሪ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ።

“ጄኔራሉን ላመሰግን እወዳለሁ ሙጋቤ ሀገሪቱን እንደቤተሰቡ ንብረት ነበር ሲገዛ የኖረው”ይላል ሌላው የዚምባብዌ ነዋሪ።

ነገሮች በቅጽበት ሊለዋወጡ በሚችሉበት በዚህ ወቅት በእርግጠኝነት ቀጥሎ የሚሆነውን መናገር አስቸጋሪ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ክብራቸውን የጠበቀ በሚመስል መንገድ ከስልጣን ለማግለል የወታደሩ ክፍል እየሰራ ይመስላል ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

የ93 አመቱ ሙጋቤ ስልጣነ መንበሩን ለሚስታቸው ግሬስ ሙጋቤ አሸጋግሮ ስርወ መንግስቱን ለማስቀጠል ያደረጉት ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

የዚምባቡዌን ሙሉ ዜግነት አግኝተው በሀገሪቱ በጥገኝነት ላይ የሚገኙት የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያምን አግኝቶ ማነጋገር ባይቻልም ስፖት ላይት ዚምባቡዌ የተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ግን በሰኔ 2016 እትሙ ስለ ኮለኔሉ መንግስቱ አንድ ዘገባ አስፍሮ ነበር።

በዘገባውም የዚምባቡዌን ሙሉ ዜግነት የያዙትና የሀገሪቱ የመከላከያ ሃይል አማካሪ ሆነው የሚሰሩት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ወታደራዊ ሃይሉ ጣልቃ በሚገባበትን ሁኔታ ላይ ከወታደራዊው መሪዎች ጋር መክረው ነበር ብሏል።

ዚምባቡዌን ካለችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለማውጣትና ሙጋቤን በጥንቃቄና በክብር ገለል ለማድረግ የወታደራዊው ክፍል ጣልቃ መግባት እንዳለበት አሁን እንቅስቃሴውን በመምራት ላይ ካሉት ጄኔራሎች ጋር ቩምባ ተብሎ በሚጠራው የእርሻ ቦታቸው ላይ መክረው እንደነበርም አስታውሷል።

ኢሳት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያምን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም አንድ የቤተሰባቸው አባል ግን እነሱ ጋር ምንም የተፈጠረ ነገር እንደሌለና የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።