በኢትዮጵያ ሶማሊያ ድንበር በተነሳው ግጭት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የገደሉዋቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል

ግንቦት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምንጮች እንደገለጹት የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያ አባላትና የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወሰዱት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል።
ሂራን በተባለው አካባቢ ለቀናት በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት መንስኤ በውል አልታወቀም። ዛሬ በማህበራዊ ድረገጾች የተላለፈው አስደንጋጭ ቪዲዮ በርካታ የሞቱ ሲቪሎችንና የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ያሳያል።
ቪዲዮውን የለቀቀው የአልጃሲራ ኒውስ ሶማሊያ ወኪል ለኢሳት እንደገለጸው በሂራን ግዛት በሁለት ጎሳ አባላት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሁለቱም ጎሳ አባላት ላይ በወሰዱት እርምጃ የሞቱት
ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። ግጭቱ አሁንም ድረስ አልበረደም። ኢሳት ከሁለት ቀናት በፊት በግጭቱ 70 ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ ነበር።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች እስካሁን የገለጹት ነገር የለም። የኢህአዴግ መከላከያ ሰራዊት አባላት በኢትዮጵያ የሶማሊ ተወላጆች ላይ ከፍተና ሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን የተለያዩ አለማቀፍ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች
ሲገልጹ ቆይተዋል።