(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2011)በአዲስ አበባ በ5 ክፍለከተሞች ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተካሄዱት ህገወጥ ግንባታዎች በባለሀብቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካኝነት መሆኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከመሬት ወረራውና ህገወጥ ግንባታው ጋር በተያያዘ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃቸው እንዳለበት ገልጸዋል። በስም እነማን እንደሆኑ ግን አልጠቀሱም።
የከንቲባው ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ክፍል ሃላፊ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ ለኢሳት እንደገለጹት እንዲፈርሱ ውሳኔ የተላለፈባቸው ህገወጥ ግንባታዎች ጉዳይ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት አይደለም።
በተለየ ሁኔታ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የመሬት ወረራ ተደርጓል ያሉት ወይዘሪት ፌቨን የከተማው አስተዳደር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ህገወጥ ወረራና ግንባታ ያደረጉ አካላት በራሳቸው ጊዜ አፍርሰው አካባቢውን እንዲለቁ ማሳሰቡን ገልጸዋል።
በቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ጉለሌና የካ ክፍለ ከተሞች የተደረጉት ወረራዎችና ግንባታዎች ይበልጥ የሚጎዱት ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነም ወይዘሪት ፌቨን ገልጸዋል።
ባለሃብቶቹና የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በተመለከተ አቃቤ ህግ ምርመራ በማድረግ ለህግ እንደሚያቀርባቸውም የከንቲባው ጽ/ቤት የፕሬስ ክፍል ሃላፊ ወሪት ፌቨን ለኢሳት ገልጸዋል።