በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በመፈጠሩ ሸማቾች መቸገራቸውን ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 06 ቀን 2010 ዓ/ም) ላለፉት ሶስት ዓመታት አገዛዙን በማውገዝ የተነሳውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ በመላው አገሪቱ የዋጋ ጭማሪና የኑሮ ውድነት በከፋ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል። በተለይም መዲናዋ አዲስ አበባ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በሸቀጦች ላይ እጥፍ የዋጋ ጭማሪና የገበያ መቀዛቀዝ መፈጠሩን የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቧል።
አንድ የከተማው ነዋሪ የሆኑ እናት ከወራት በፊት የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ በመደረጉ ከቤት አከራይ ጀምሮ ሁሉም የንግድ ማህበረሰብ ከፍተኛ ዋጋ ጨምረዋል። የእለት ጉርስ ለመሸፈን እንኳ ፈተና እንደሆነባቸውና የኑሮ ውድነቱ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ያልጨመረ ነገር የለም። በተለይ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚታየው ጭማሪ እስከዛሬ ታይቶ ከሚታወቀው በላይ ነው፡፡ የበርበሬና የሽሮ እህሎች ዋጋ ከሚጠበቀው በላይ ጨምሯል። በኪሎ 70 ብር ይሸጥ የነበረው በርበሬ አሁን 130 ብር ሆኗል። በተመሳሳይ በባቄላና አተር ላይ ከ20 ብር ያላነስ ጭማሪ ታይቷበተታል ብለዋል።
በአገር ውስጥ ምርት ላይ ምን ተአምር ስለተፈጠረ ነው በአንድ ሳምንት በዚህ መጠን የሚጨምረው? ሲሉ ቸማቾቹ ጠይቀዋል። ነጋዴዎቹ በበኩላቸው እኛ ምን እናድርግ ከመርካቶ ያመጣነው በውድ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣሉ።
በሸቀጣሸቀጥ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ጭማሪ ከወትሮ የተለየና የተጋነነ መሆኑን ነጋዴዎቹ ይናገራሉ። ከሁለት ሳምንት በፊት 32 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና አሁን 38 ብር ገብቷል። ከዚህ ቀደም 10 ብር የነበረው ሳሙና አሁን 13 ብር ነው። በፓስታ ምርት ላይም እጥፍ ጭማሪ ታይቷል ብለዋል።
መርካቶ ውስጥ ያሉ አከፋፋዮች በበኩላቸው የግብር እና የውጭ ምንዛሪ ጭማሬ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የመንገድ መዘጋት የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምሩ እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ።
አንድ ሸማች ያጋጠማቸውን ሲናገሩ «ከሳምንት በፊት 20 ፍሬ የሚይዘው አንዱ እሽግ ፓስታ 205 ብር ነበር፣ ከአከፋፋዮቹ የገዛሁት። ዛሬ ግን 305 ብር መድረሱን ስሰማ መግዛቴን ትቼ ተመልሻለሁ» ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ነጋዴው የቤት ኪራይ መክፈል እስከሚያቅተው ድረስ ተቸግሯል። በሰዓታት ልዩነት ያለገደብ በሸቀጣሸቀጥ ላይ የሚደረገው ጭማሬ ስላስፈራቸው እቃ ከማምጣት መቆጠባቸውን ነጋዴዎቹ ይገልጻሉ፡፡ «የዋጋ ጭማሪው ስላማረረኝ እቃ ማምጣት አቁሜያለው፣ ሱቄም ባዶ እየሆነ ነው» በማለት ነጋዴው ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል።