የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት “አድልዎ ተፈጽሟል” በማለት አድማ መጀመራቸውን ተሰማ

የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት “አድልዎ ተፈጽሟል” በማለት አድማ መጀመራቸውን ተሰማ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 06 ቀን 2010 ዓ/ም) ፖሊሶቹ አድማውን የሚያደርጉት ቢሮአቸው ውስጥ ያለ ስራ በመቀመጥ መሆኑን የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል። የአድማው መነሻ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንደማይሰጣቸው መታወቁን ተከትሎ ነው። የከተማው አስተዳደር የልዩ ሃይል እና የፖሊስ አባላት መሬት እንደሚሰጣቸው ከገለጸ በሁዋላ፣ ረዳት ኮሚሽነር ደስዬ ደጀኔ ለከተማ አስተዳደሩ ትዕዛዝ በመስጠት ቦታ እንዳናገኝ አስከልክሎናል በሚል አድማ መጀመራቸውን ምንጮች ተናግረዋል።
አድማውን የሚያስተባብሩ አካላት “ እኛ መሬት ለማግኘት ስንል ግደሉ ስንባል መግደል?” አለብን ወይ በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ “ መሬት ለማግኘት ስንል ህዝብን አንጨፈጭፈም” የሚል አቋም በመያዛቸው ከአዛዦች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት በሚል የተወሰኑ ሰዎች እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የክልሉ ፖሊሶች ከዚህ ቀደም የህወሃት የበላይነት ይብቃ በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር መዘጋቡ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደታወጀ፣ የክልሉን ፖሊስ እንደገና የማደራጀት ስራ ተሰርቷል። የህወሃትን የበላይነት ይቃወማሉ የተባሉ የፖሊስ አዛዦች ከስራ እንዲባረሩ ወይም እንዲታሰሩ ተደርጓል።