ሰኔ ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በክረምት መጠለያ አልባ የሆኑት የቀድሞ የሃና ማርያም አካባቢ ነዋሪዎች፣ ቤት ለመከራዬት እንኳን ስንጠይቅ፣ አከራዮቹ “ ‘እንዳታከራዩዋቸው’ የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል” በሚል ቤታቸውን ሊያከራዩን ፈቃደኞች አልሆኑም ሲሉ ብሶታቸውን ገልጸዋል።
ገዢው መንግስት ወጣቶችን እያደነ ማሰሩን መቀጠሉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በእስር እና በግድያ መበቀሉ አንሶ አሁን ደግሞ ቤት እንዳንከራይ በመከልከል የበቀል ጅራፉን እያሳረፈብን ነው ይላሉ። ከቀርሳ ኮንቶማ የመጡትን ወጣቶች እየፈለጉ በማሰር ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የፌደራል ፖሊስ አካባቢውን አሁንም ድረስ በመቆጣጠሩ መግባት መውጣትም አልቻሉም። በአካባቢው ያለው አርሶአደር የተፈናቀሉትን ሰዎች እየቀለበ መሆኑንም ነዋሪዎች ገልጸዋል። ለኢሳት የደረሱት ፎቶግራፎች እንደሚያሳዩት በህመም የሚሰቃዩ አቅመ ደካማ አሮጊቶችና አራሶችና ሳይቀሩ በግዴታ ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርጓል።
የክረምቱ ዝናብ ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ አውድሞታል። መስተዳድሩ የወሰደው እርምጃ በ21ኛው ክፈለዘመን ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ነው ሲል ወኪላችን ዘገባውን አጠቃሏል።