የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች በወታደሮች ሲዋከቡ ዋሉ

ሰኔ ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፋብሪካው ሰራተኞች ለጂንካ ልማት በሚል ያለፈቃዳቸው ከደሞዛቸው እየተቆረጠ መከፈሉን ሲቃወሙ የሰነበቱ ሲሆን ዛሬ ከ200 በላይ ወታደሮች ወደ ፋብሪካው በመግባት ሰራተኞችን ሲያስጨንቁ ውለዋል።

ከደርጃ 1-13 የሚገኙ ሰራተኞች  በአንድ ድምጽ “አንከፍልም” በማለት ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውን ተከትሎ በብሄር እየለዩ ለማጋጨት ሙከራ ሲደረግ መሰንበቱን ሰራተኞች ገልጸዋል። የአማራ ተወላጆች  “ልማት አደናቃፊ እና የድሮ ሥርዓት ናፋቂ “ እየተባሉ ሲዋከቡ የቆዩ ሲሆን የኦሮሞ ተወላጅ ሰራተኞችም እንዲሁ በተቃዋሚነት ተፈርጀው ተዋክበዋል። ማኔጅመንቱ ሰራተኛውን ሳያስፈቅድ ለጅንካ ከተማ ልማት  1.5 ሚሊየን ብር እንከፍላለን ብሎ ቃል መግባቱ የችግሩ መነሻ መሆኑን ሰራተኞች ይናገራሉ።

ከደርጃ 1-27 የሚገኙት ያለ ፍላጎታቸው የድርጅት አባል ናችህ በሚል ብቻ ከደሞዛቸው 10 በመቶ የተቆረጠባቸው ሲሆን፣  ሰራተኞቹም ጥያቄ ሲያነሱ የኢህአዴግ አባል ካልሆንክ የደረጃ እድገት አታገኝም የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ኦሞ ኩራዝ እና የጣና በለስ ስካር ፋብሪካዎችን የመከላከያ ብርታብርት ኢንጅነሪንግ ሜቴክ እና መሥፍን ኢንጅነሪንግን የመሳሰሉ የህወሃት ኩባንያዎች የሚሰሩት ሲሆን፣ ዋና ዋና የአመራር ቦታዎች በህወሃቶች የተያዘ ነው። የአካባቢው ተወላጆች ከስኳር ፋብሪካ ግንባታው ተጠቃሚ አይደለንም በማለት ቅሬታ ያሰማሉ። ተቃውሞውን በመፍራት ይመስላል የአካባቢው ተወላጆች እየተባረሩ የጉልበት ሰራተኞች ከአንድ አካባቢ ብቻ እንዲመጡ እየተደረገ መሆኑን ሰራተኞች ይገልጻሉ። የመከከላከያ ሰራዊት አባላት በማስፈራራት ሰራተኞች ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት እስካሁን አልተሳካም።