በአውሮጳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጄኔቭ የተባበሩት መንግሥታት ዋና መ/ቤት ፊት ለፊት የሕዝብ ትዕይንት አደረጉ

ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን በዛሬው ዕለት በጄኔቭ ስዊትዘርላንድ የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን በአማሮች ላይ የደረሰውን መፈናቀል የሚያሳይ የጽሑፍ፣ የድምፅና የምስል ማስረጃ ለሦስት ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ማስረከባቸውንም ባልደረባችን ወንድምአገኝ ጋሹ ከሥፍራው ዘግቧል።

ከቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል በቅርቡ የተፈናቀሉትን አማሮች ሁኔታ በዋናነት በማንሳት ባለፉት 22 ዓመታት በሀገሪቱ የቀጠለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ በማውሳት የተቃውሞ ድምፃቸውን ያስተባበሩት ኢትዮጵያውያን ትዕይንተ ሕዝቡን ባዘጋጀው ግብረ ኃይል አባላት አማካኝነት ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለዓለም ዐቀፍ ቀይ መስቀል እንዲሁም ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በሰነድ የተደገፈ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

በጽሑፍ፣ በምስል እና በድምፅ የተደገፈውን ማስረጃቸውን ለተዘረዘሩት ተቋማት ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን በጎ ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ዓለም ዐቀፉ ቀይ መስቀል የአፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያውያኑን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፤ ተፈናቃዮቹ መልሰው በሚታተሙበት ሁኔታ ላይ በሀገር ቤት ካሉት ወኪሎቻቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ገልፀዋል።

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ዋና ዳይሬክተርና ትዕይንተ ሕዝቡን ያስተባበረውን የኢትዮጵያውያኑን ግብረ ኃይል ያነጋገሩ ሲሆን፣ አዎንታዊ ምላሽ በመሥጠት ተፈናቃዮቹን ለመታደግ ያላቸውን ዝግጁነት እንደገለፁም ተመልክቷል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ግብረ ኃይሉ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር ያደረገውን ቆይታ የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ማግኘት አልቻልንም።