አንድነት መግለጫ አወጣ

ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነአንዱዓለም አራጌና በናትናኤል መኮንን የቀረበውን ይግባኝ ውድቅ ማድረጉ በፍትሕ ተቋማት ላይ እምነት መጣል እንደማይቻል ማሳያ ነው ሲል አንድነት ፓርቲ ገለጠ። በፋሲካ በዓል እስረኞቹን ለመጎብኘት የሞከሩት የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላትም በልዩ ኃይል ተባረሩ።

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ገዢው ፓርቲ በማን አለብኝነት የፓርቲው አመራሮችን አስሮ የሚሠራው ሽፍጦች ትግሉን የበለጠ የሚያጠናክሩ እንጂ አንገታችንን የሚያስደፉ አይደለም ብሏል።

በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላይ ያደረገው ጥናት ላይ“በከፍተኛ የሕዝብ አመኔታ ያጡ ተቋማት” በሚል ርዕስ ስር በመጀመሪያ የተቀመጡ ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን የጠቀሰው የአንድነት ፓርቲ መግለጫ ከነዚህ አይነት ፍርድ ቤቶች ፍትሕ መጠበቅ አዳጋች ነው ብሏል።

የሕዝብ አመኔታ ያጡ ተቋማት ተብለው በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡት የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ፍትሕ ማግኛ ሳይሆኑ የገዢው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚዎች ናቸው ብሏል የአንድነት ፓርቲ ይፋ መግለጫ።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አንዱዓለም አራጌና ናትናኤል መኮንን በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሽብርተኝነትን እንደሚያራምዱ ተደርጎ ያቀረበው ሀተታ የፓርቲውን ጠንካራ መዋቅር ያላገናዘበ ከመሆኑ በላይ መልካም ስሙን የሚያጠፋ ነው ብሏል።

የአንድነት ፓርቲ መግለጫ “አንዱዓለም አራጌና ናትናኤል መኮንንም ሆኑ ሌሎች አባላቱ ሰላማዊ ታጋዮች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም” ሲል አስታውቋል።