ሰማያዊ ፓርቲ በ አፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት ፊትለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ አቀረበ

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአብዛኛው በወጣቶች እና በሴቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ  እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጪው ሜይ 25  በ አፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ ህዝባዊ ጥሪ አስተላለፈ።

የተቃውሞ ሰልፉ የሚደረገው የ አፍሪካ ህብረት 50ኛ ኣመት  በ ዓሉን በሚያከብርበት ዕለት ነው።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰቡ ተቋማትና ኢትዮጵያውያን ሁሉ በህጋዊውና ሰላማዊው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዲሳተፉ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

ድርጅቱ በመግለጫው ” ለፍትህና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የሚታገሉ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን በአሸባሪነት ስም ማሰርና ማሰቃየትን እንዲቆም ቢጠይቁም መልስ ያልተገኘ መሆኑን፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብቶችን በመጣስ ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ኢሰብዓዊ በሆነ ድርጊት በታጠቁ ኃይሎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተፈናቀሉት ዜጎችም በአስቸኳይ ወደ የመኖሪያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ በመንግስትም ሆነ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ቢጠይቅም መልስ አለማግኘቱንና ፣  አሁንም ገና የሚፈናቀሉ ዜጎችን ስም ዝርዝር በየማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ተለጥፎ ማየቱ፣  መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ፣ የእምነት ስርዓታችንና የሃይማኖት መሪዎቻችንን እምነታችን በሚፈቅደው ብቻ እናከናውን ያሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን በአሸባሪነት ወንጀል በመክሰስ በእስር እንዲማቅቁና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ በማድረጉና ችግሩን ለማስተካከል የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ እንዲሁም  መንግስት የኑሮ ዉድነትን፣ የሥራ አጥነትንና በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ሌቦችን የሚቆጣጠርባቸውን መንገዶችና ፖሊሲዎች በማዉጣት ሐገራችንን ከቀውስና ዜጎችንም ከሰቆቃ እንዲያወጣ በተደጋጋሚ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ሰሚ አጥተው በመቆየታቸው” ሰለማዊ ሰልፍ ለመጥራት መገደዱን ገልጿል።

ፓርቲው ” ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ሐገራትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች በሚገኙበት ድምፃችንን ለማሰማት ከግንቦት 15 – 17 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ጥቁር ልብስ በመልበስና ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ከላይ ያነሳናቸውና ሌሎችም ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ” እንጠይቃለን ብሎአል ። እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሲቪክ ማህበራትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በእነዚህ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡን አስታውቋል።

ድርጅቱ እንዳሰበው ሰለማዋ ሰልፍ ማድረግ ከቻለ ከምርጫ 97 ወዲህ መንግስትን በመቃወም የተደረገ የመጀመሪያው ሰላማዊ ሰልፍ ይሆናል።

በአገር ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰላማዊ ሰልፎችን በመጥራት ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ ድፍረቱ የላቸውም እየተባሉ በተደጋጋሚ ይተቻሉ። አንድነት ፓርቲን ጨምሮ የ2002ትን ምርጫ ያልተሳተፉ ፓርቲዎች ፣ ተቃውሞአቸውን ለመግልጽ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠሩ አስታውቀው ነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ሳይተገብሩት ቀርተዋል፤ ለምን እንዳልተገበሩትም ማብራሪያ እስካሁን ድረስ አልሰጡም።