የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ኩባንያን ካሳ እጠይቃለሁ አለ

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አየር መንገዱ ካሳ የሚጠይቀው ከአምስት ወራት በፊት አዲስ ያስገባቸው ቦይንግ 787 አውሮፕላኖች  ብዙም አገልግሎት ሳይሰጡ ከበረራ ውጭ ተደርገዉ የቆዩ በመሆኑ ነዉ ፡፡

አውሮፕላኖቹ በረራ አቁመው የነበረው በባትሪያቸዉ ላይ ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት በአሜሪካ የፌደራል የበረራ መስሪያ ቤት እገዳ ስለተጣለባቸዉ እንደነበር መዘገቡ  ይታወሳል፡፡

የኢትዮዽያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ፥ ከዚህ በፊት ትኩረታችን አውሮፕላኖቹን ወደ በረራ መመለስ የነበረ ሲሆን ፤ የሚቀጥለው ሥራችን ደግሞ ከቦይንግ ካሳ የምናገኝበትን መንገድ መፈለግ ነዉ ሲሉ ለፋና ራዲዮ ተናግረዋል፡፡

ከ አፍሪካ  ቦይንግ ድሪም ላይነር አውሮፕላን በክፍተኛ የብድር ገንዘብ የገዛችው አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት።

አውሮፕላኑ በተገዛ ማግስት ብዙም ሳያገለግል በቴክኒክ ችግር ሳቢያ እንዲቆም ትዕዛዝ የተላለፈበት ድሪም ላይነር ከወራት በሁዋላ ሰሞኑን የሙከራ በረራ ወደ ናይሮቢ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ለደረሰው የወራት ኪሳራ ካሳ እጠይቃለሁ ማለቷን አስመልክቶ እስካሁን  ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በኩል የተሰማ  ነገር የለም ፡፡