ሐምሌ ፭( አምት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በሁለቱ ከተሞች በተካሄዱት ስብሰባዎች ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተሰቃየ እንደሚገኝ በድፍረት ለመንግስት ተወካዮች ሲገልጽ ተሰምቷል።
በእንጅባራ አንድ ነጋዴ ሲናገሩ የመንግስት ባለስልጣናት የሚያቀረቡዋቸው ሪፖርቶች ለራሳቸው የሚጠቅሙ እንጅ ህዝቡ የሚያያቸው አይደሉም በማለት በማስረጃ አስደግፈው አቅርበዋል። ነጋዴው እንዳሉት እቃዎች ሳይገዙ እንደተገዙ ተደርጎ ይወራረዳሉ፣ ጥራት ያላቸው እቃዎች አይገዙም፣ የመንግስት መጋዘኖችም በባለስልጣናት ይዘረፋሉ።
የከተማዋ ባለስልጣናት ከሙስና እና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ክሶች ሲቀርቡባቸው እርምጃ ከሚወሰድባቸው ይልቅ ወደ ሌሎች መስሪያቤቶች ተዛውረው እንዲሰሩ እንደሚደረጉ ነጋዴው ገልጸው፣ ተቃውሞአቸውን በሚያሰሙበት ጊዜም አሻባሪዎች፣ ጸረ ህዝቦች እየተባሉ እንደሚከሰሱ የራሳቸውን ገጠመኝ በመጥቀስ በምሬት ተናግረዋል :: አንድ ነዋሪ ደግሞ “የመገናኝ ብዙሀን ችግራችንን አይዘግቡም፣ እንዳይዘግቡም ይደረጋሉ” በማለት በመገናኛ ብዙሀን ላይ የሚደርሰውን አፈና በዝርዝር አቅርበዋል ::
“ጥቃቅንና አነስተኛ መንግስት ነጋዴውን ከህዝቡ ጋር ለማጋጨት” ተብሎ የተነደፈ ይመስለኛል በማለት በስብሰባው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማ ነዋሪም ነበሩ ::
በጉዳዩ ዙሪያ የእንጅባራን አስታዳዳሪ ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።