በ1976 ዓ.ም የተቋቋመው አንጋፋው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ማኔጅመንት ከሠራተኛው ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ ገባ

ሐምሌ ፭( አምት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በሀላፊነት ላይ የሚገኙ የድርጅቱ  ሠራተኛ እንደተናገሩት በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሙክታር ከድር በቦርድ ሰብሳቢነት ወደመድን ድርጅት ከመጡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ዘረኝነትና ግልጽ የሆነ ዘረፋ በድርጅቱ ውስጥ በመንሰራፋቱ  በርካታ ባለሙያዎች ድርጅቱን ለመልቀቅ እየተገደዱ ነው።
ችግሩን ቦርዱ ተመልክቶ ሠራተኛውን እንዲያወያይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም እነአቶ ሙክታር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በአሁኑ ወቅት ህልውናው ጭምር በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፤ አብዛኛው ሠራተኞች ቅሬታ ውስጥ በመሆናቸው የዚህ ዓመት የሥራ ዕቅድ በአብዛኛው ቅርንጫፎች እንዳልተሳካ ጠቁመዋል፡፡

በድርጅቱ የሰፈነው ዘረኝነት ዓይን ያወጣ በመሆኑ ይህም አብዛኛውን ሠራተኛ በማስከፋቱ በአገልግሎት አሰጣጡም ላይ አሉታዎ ተጽዕኖን ፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ነባር ደንበኞች የኢንሹራንስ የኮንትራት ጊዜያቸውን ማራዘም በመተው ወደ ግል
ኢንሹራንስ ድርጅቶች ጥለው ለመሄድ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

መ/ቤቱ በነገው ዕለት በችግሮቹ ላይ ለመወያየት በአምባሳደር ሲኒማ አዳራሽ ጠቅላላ የሠራተኞች ስብሰባ መጥራቱን የድርጅቱ ምንጮች ጠቁመው ይህ ስብሰባ ሠራተኛው ከማኔጅመንቱ ጋር ፊት ለፊት የሚፋጠጥበት ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ድርጅቱ ባለፈው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 149 ሚሊየን ብር ማትረፉን ይፋ አድርጎ ነበር።