በአንድ አመት ከስድስት ወር ይጠናቀቃሉ ተብሎ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የወጣባቸው የስኳር ፕሮጀክቶች ከ6 አመታት በሁዋላም አልተጠናቀቁም
( ኢሳት ዜና ጳግሜን 02 ቀን 2010 ዓ/ም ) በቀድሞው የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ጸሃዬ እና በሜቴክ የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው መካከል የተፈረመው የውል ሰነድ እንደሚያሳየው ከፍተኛ ሃብት የፈሰሰባቸው 10 የስኳር ፕሮጀክቶች በ2005 እና በ2006 ምርት ማምረት ነበረባቸው። ይሁን እንጅ አንዱም ፋብሪካ እስካሁን ማምረት አልጀመረም።
ውሉ እንደሚያስረዳው እያንዳንዱ የስኳር ፋብሪካ የቫት ክፍያን ሳይጨምር 216 ሚሊዮን 750 ሺ የአሜሪካን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ሲሆን፣ ሜቴክ ለመጀመሪያዎቹ 3 ፋብሪካዎች ግንባታ 650 ሚሊዮን 250 ሺ የአሜሪካን ዶላር ይከፈለዋል። ሜቴክ እነዚህን ፋብሪካዎቸ በ1 አመት ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ማስረከብ ቢኖርበትም ከ5 አመታት በሁዋላም ለማስረከብ አልቻለም። የሌሎቹ 7 ፋብሪካዎች የአከፋፈል ሁኔታ ደግሞ እንዳጀማመራቸው እንደሚከፈልና ሜቴክ የብዙዎችን ክፍያ እንደወሰደ ያመለክታሉ።
ከሰም መጋቢት 2004 ዓም ተጀምሮ ነሃሴ 2005 ዓም እንደሚጠናቀቅ፣ በለስ ቁጥር 1 መጋቢት 2003 ዓም ተጀምሮ ነሃሴ 2005 ዓም እንደሚጠናቀቅ ፣ በለስ ቁጥር 2 መጋቢት 2003 ዓም ተጀምሮ ነሃሴ 2005 ዓም እንደሚጠናቀቅ በውሉ ላይ ተገልጿል። ወልቃይት ቁጥር አንድ መስከረም 2004 ዓም ተጀምሮ መጋቢት 2005 ዓም ፣ ኦሞ ቁጥር 1 እና ቁጥር ሁለት መስከረም 2004 ተጀምረው መጋቢት 2005 ዓም መጠናቀቅ ነበረባቸው። ኦሞ ቁጥር 3 ደግሞ ጥር 2004 ኣም ተጀምሮ ሃምሌ 2005 ኣም መጠናቀቅ ነበረበት። ኦሞ ቁጥር 4 ፣ ቁጥር 5 እና ቁጥር 6 ጥር 2004 ዓም ተጀምረው ሃምሌ 2005 መጠናቀቅ ነበረባቸው።
ፋብሪካዎቹ እያንዳንዳቸው በቀን 250 ሺ ቶን ስኳር የማምረት አቅም እንደሚኖራቸው በስምምነቱ ላይ ተገልጾ ነበር። ሜቴክ አንዱንም ፋብሪካ ገንብቶ ሳያስረክብ ስራው ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ከሜቴክ ተቀምተው ለውጭ አገር ኩባንያዎች ተሰጥተዋል። ሜቴክ ላወደመው የአገር ሃብት እስካሁን ተጠያቂ የሆነ አካል የለም።