የአባይ ግድብ ዋና መሃንዲስና መሪ ኢንጂነር ስመኛው በቀለ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ፖሊስ አስታወቀ

የአባይ ግድብ ዋና መሃንዲስና መሪ ኢንጂነር ስመኛው በቀለ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ፖሊስ አስታወቀ
( ኢሳት ዜና ጳግሜን 02 ቀን 2010 ዓ/ም ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል በመሩት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ፖሊስ ኢንጂነር ስመኛው ራሳቸውን አጥፍተዋል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የተለያዩ ማስረጃዎችንና የጥናት ዘዴዎችን መጠቀማቸውን የገለጹት መርማሪ ፖሊሶቹ፣ ለዚህ ድምዳሜ ያደረሱዋቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች ከመሞታቸው በፊት የተጻጻፉዋቸው ደብዳቤዎች፣ ከአሟሟታቸው ሁኔታና ከመኪና ቁልፍ ጋር የተያያዘ ነው።
ፖሊስ እዚህ ድምዳሜ ላይ ቢደርስም፣ “ ኢንጂነሩ ለምን ራሳቸውን አጠፉ?” የሚለውን ጥያቄ በአሁኑ ሰዓት ለመመለስ እንደማይችል ኮሚሽነሩ ዘይኑ ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት ግድያው ከስራቸው ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
ነሃሴ 19 ቀን 2010 ዓም ህይወታቸው አልፎ የተገኙት ኢንጂነር ስመኛው የአሟሟታቸው ሁኔታ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ይዞ ቆይቷል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰጡት አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት በርካታ ኢትዮጵያውያን የፖሊስን ሪፖርት በጥርጣሬ አይን ያዩታል።